Search

ብሪክስ፡ በዓለም አቀፉ የኃይል ሚዛን ውስጥ የተከፈተ አዲስ ምዕራፍ

እሑድ መስከረም 03, 2019 105

ዓለም አቀፉ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አሰላለፍ ከአንድ ቡድን የበላይነት በመውጣት ባለብዙ ወገን ወደሆነ አዲስ የኃይል ሚዛን እየተሸጋገረ ይገኛል።

የዚህ አዲስ ዓለም አቀፍ ትስስር ማዕከል የሆነው የብሪክስ ጥምረት ዲፕሎማቶች የሚሰባሰቡበት መደበኛ መድረክ ሳይሆን የዓለምን የሰው ኃይል፣ የአምራችነት አቅም እና የቴክኖሎጂ የበላይነት የተቆጣጠሩ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች ስብስብ ነው።

ይህ ጥምረት የዓለም የአምራችነት እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሞተሯን ቻይና፣ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የበለጸገች የቴክኖሎጂ ማዕከሏን ሕንድ እንዲሁም በኃይል ማመንጨት እና በሳይንስ ጥናት ቀዳሚዋን ሩስያ አቅፏል።

ብራዚል በግብርና ቴክኖሎጂና በታዳሽ ኃይል የዓለም ዋነኛ ተወዳዳሪ ስትሆን፣ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በማዕድን እና በፋይናንስ ዘርፍ የጎላ ድርሻ አላት።

ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ግብጽ እና ኢራን መቀላቀል ጋር ተዳምሮ ጥምረቱ የዓለምን ግማሽ ያህል ሕዝብ የሚወክል እና በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ አምራች ዜጎችን በአንድ ጥላ ስር ያገናኘ ግዙፍ የገበያ ማዕከል ሆኗል።

ኢትዮጵያ ይህን በቴክኖሎጂ እና በኢኮኖሚ ግንባር ቀደም የሆኑ አጋሮችን ስብስብ ስትቀላቀል፣ ለብሔራዊ ጥቅሟ የሚያስገኘውን ትልቅና ተጨባጭ ፋይዳ በመገንዘብ ነው።

ከአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ሁለተኛ፣ የአህጉሪቱ የፖለቲካ ማዕከል እንዲሁም ሰፊ አምራች ኃይል ያላት በመሆኗ ኢትዮጵያ ለብሪክስ ስትራቴጂያዊ በር ስትሆን፤ ጥምረቱ ደግሞ ለኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ሽግግር አቅም ፈጣሪ ነው።

ከቻይና እና ከሕንድ የላቀ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተሞክሮ በመውሰድ የሳይበር ደኅንነት እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ልምዶችን፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን እና የኮደርስ ንቅናቄን በከፍተኛ ፍጥነት ለማሳደግ ያስችላል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ ለልማት የሚውል የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ከሩስያ ጋር የጀመረችው ትብብር፣ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን በማረጋገጥ የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ለማፋጠን ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

ከቴክኖሎጂ ሽግግር በተጨማሪ ማኑፋክቸሪንግን በማዘመን የተፈጥሮ ሀብትን እና የሰው ኃይልን ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ዕድል ይከፍታል።

በአብዛኛው ወጣት የሆነው የሀገራችን አምራች ኃይል የሚያመርታቸውን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ወደ ብሪክስ አባላ ሀገራት ግዙፍ ገበያዎች ያለ ከባድ መሰናክል ለመላክ የሚያስችል ሰፊ የገበያ ትስስር ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ ይህን ጥምረት መቀላቀሏ ከተበዳሪነት እና የዕርዳታ ተቀባይነት ትርክት ወጥታ የዓለምን የቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ አጀንዳ ከሚቀርጹ ታላላቅ ኃይሎች ጋር በእኩልነት የምትሰለፍበትን ታሪካዊ ምዕራፍ ከፍቷል።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: