ዓለም አቀፉ የጂኦፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ምህዳር በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የተስፋፋው የብሪክስ ኅብረት የዓለምን የኃይል እና የኢኮኖሚ ሚዛን በአዲስ መልክ የሚቀይር አንቀሳቃሽ ሞተር ሆኖ ወጥቷል።
በሕንድ ኒው ዴልሂ “የመቋቋም አቅምን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ደግሞ፣ ይህንን ትስስር ይበልጥ በማጠናከር የባለብዙ ወገን ሥርዓት የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ክስተት ነው።
ኢትዮጵያ የዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኅብረት አባል እንደመሆኗ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው ልዑክ በጉባኤው እያደረገው ያለው ሰፊ ተሳትፎ እና የጎንዮሽ የዲፕሎማሲ ውይይቶች ለሀገራችን አዲስ የኢኮኖሚ ዕድል በሩን የከፈቱ ናቸው።
ብሪክስ አሁን ላይ ከዓለም ሕዝብ ግማሽ ያህሉን የሚወክል እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያላቸውን ታዳጊ ሀገራት ያቀፈ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በዚሁ መድረክ ያላትን ተሳትፎ ማጠናከሯ የላቀ ስትራቴጂካዊ ትርጉም አለው።
በኒው ዴልሂ ጉባኤ ላይ በስፋት እየተነሱ ያሉት የፋይናንስ፣ የንግድ እና የቴክኖሎጂ ትብብር ማዕቀፎች ኢትዮጵያ ከአባል ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ እና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ እንድታሳድግ ያስችሏታል።
የኢንቨስትመንት አድማስ መስፋፋትን በተመለከተ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እና በማዕድን ዘርፎች ሰፊ የገበያ መዳረሻን ይፈጥራሉ።
ከዚህም ባሻገር የአዲሱ ልማት ባንክ (NDB) ተጠቃሚ በመሆን፣ ለግዙፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ ለመንገድ፣ ለኃይል ማመንጫዎች እና ለኮሪደር ልማቶች የሚሆን የፋይናንስ አማራጮችን ለማስፋት ምቹ መደላድል ያመቻቻል።
በታሪክ የፓን-አፍሪካኒዝም ማዕከል እና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በጉባኤው የምታደርገው ተሳትፎ የአፍሪካን ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ ነው።
የደቡብ-ደቡብ ትብብርን በማጠናከር፣ ታዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ፍትሃዊ ተሳታፊ እንዲሆኑ የምታደርገውን ጥረት በተግባር ያሳያል።
በጉባኤው መሪ ቃል ውስጥ የሰፈረው የ“ፈጠራ እና ዘላቂነት” አጀንዳ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ማሻሻያዎችን እያደረገችባቸው ካሉ የዲጂታል ኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ሥራዎች ጋር በቀጥታ የሚጣጣም ነው።
ጉባኤው የኢትዮጵያን እና የኅብረቱን ትስስር የበለጠ በማጠናከር የወደፊት የጋራ ዕድገትን፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን እና የተጠናከረ የዲፕሎማሲ አቅምን የሚያረጋግጥ ስልታዊ እርምጃ ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: