ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) ጥምረት አባል መሆኗ ከፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድልነቱ ባሻገር የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ ዕድሎችን አሟጥጦ ለመጠቀም የሚያስችል ሰፊ አዲስ የኢኮኖሚ መድረክ ከፍቶላታል።
በተለይም ከግዙፍ እና በፍጥነት እያደጉ ካሉ የዓለም ኢኮኖሚዎች ጋር ያላትን ትሥሥር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አባል ሀገራቱ የንግድ ልውውጣቸውን በየራሳቸው ገንዘቦች (Local Currencies) ለማካሄድ እና የድንበር ተሻጋሪ ክፍያዎችን ለማቀላጠፍ የጀመሩት ጥረት ለኢትዮጵያ ልዩ ዕድል የሰጠ ነው።
ይህ ቀልጣፋ የክፍያ ሥርዓት የንግድ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ፣ የሀገራችን ላኪዎች እንደ ቡና፣ የግብርና ምርቶች፣ ጨርቃጨርቅ፣ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች፣ እንዲሁም ማዕድናትን ወደ ሰፊው የ'ብሪክስ' ገበያ በቀላሉ እንዲያቀርቡ አዳዲስ የገበያ በሮችን ይከፍታል።
ሆኖም ይህንን ወርቃማ ዕድል ወደ መሬት ለማውረድ የምርት ጥራትን፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እና አስተማማኝ የአቅርቦት አቅምን ማሳደግ የግድ ይላል።
ከገበያ ትሥሥር ባለፈ፣ ብሪክስ ለኢትዮጵያ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ምንጭም ነው። የአባል ሀገራቱን ካፒታል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የላቀ የገበያ ልምድ ከኢትዮጵያ እምቅ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ጋር በማስተሣሠር፣ በአምራች ዘርፍ፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር፣ በኢነርጂ፣ በሎጂስቲክስ፣ በማዕድን እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች ሰፊ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር ቁልፍ ሞተር ነው።
የጥምረቱ የፋይናንስ ትሥሥር በትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ብቻ የሚገደብ አይደለም። አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተሻለ የብድር እና የፋይናንስ ተደራሽነት በማግኘት፣ ምርታቸውን አሳድገው ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲቀላቀሉ ያግዛቸዋል።
ይህም ብሪክስን ከግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች አሻግሮ ከወጣት ሥራ ፈጣሪዎች እና ከአነስተኛ አምራቾች ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ያደርገዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የብሪክስ አዲሱ የልማት ባንክ (New Development Bank) በሀገራችን ለሚከናወኑ የኢነርጂ፣ የትራንስፖርት፣ የውኃ እና የዲጂታል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አስተማማኝ የፋይናንስ አማራጭ ሆኖ ብቅ ብሏል።
በአጠቃላይ፣ የብሪክስ አባልነት ለኢትዮጵያ ከስም ማዕረግ የዘለለ ተጨባጭ ትርጉም አለው። የሀገራችንን ምርት ከአዳዲስ ገበያዎች፣ የግሉን ዘርፍ ከካፒታል እና ቴክኖሎጂ፣ የልማት ፕሮጀክቶችን ከፋይናንስ፣ እንዲሁም አነስተኛ ንግዶችን ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር የሚያስተሣሥር ወሳኝ መድረክ ነው።
ይህንን ዕድል ለመጠቀም ሀገራችን የምርት አቅሟን ማሳደግ፣ የንግድ ሥርዓቷን ይበልጥ ማቀላጠፍ፣ የግሉን ዘርፍ ማጠናከር እና የኢንቨስትመንት ምኅዳሯን ማሻሻል ይጠበቅባታል። ይህ፣ ከአባልነት ስም ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ትርፍ የምናደርገው ወሳኝ የቤት ሥራችን ነው።
በኢንትሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: