Search

የዜሮ ድምር ፖለቲካ ማክተሚያ፡ የኢትዮጵያ የመግባባት ዴሞክራሲ ጉዞ

ማክሰኞ መስከረም 05, 2019 66

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ለዘመናት የአንዱን ማሸነፍ በሌላው መሸነፍ ላይ መስርቶ የኖረ አጥፊ ሥርዓት ነበር።

አንዱ ወገን የበላይነቱን ለማረጋገጥ የሌላኛውን ህልውና በሚያሳንስበት የዜሮ ድምር አካሄድ ኢትዮጵያ ካሏት አያሌ ኅብረ ብሔራዊ ጸጋዎች ይልቅ የእርስ በርስ መጠፋፋት እና የጥርጣሬ አጥር ሲገነባ ቆይቷል።

ይህ የፖለቲካ ሥርዓት ከሕዝቡ ወርቃማ የአብሮነት ባህል ጋር የማይናበብ እና ልዩነትን እንደ ትግል ስልት የሚጠቀም በመሆኑ ታሪካዊ ቁርሾዎችን እየፈጠረ ለዘመናት አሳሳቢ ፈተና ሆኖ ኖሯል።

በአሁኑ ወቅት ግን ኢትዮጵያ ከዚህ አጥፊ የፖለቲካ አዙሪት በመውጣት፣ ሁሉንም አካታች ወደሆነው እና በውይይት ላይ ወደተመሰረተው የመግባባት ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ጥልቅ ተቋማዊ ለውጦችን እያደረገች ትገኛለች።

ይህንን ራዕይ መሬት ለማውረድም ነፃ እና ገለልተኛ የሆኑ እንደ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያሉ ተቋማትን አዋቅራ ወደ ሥራ ገብታለች።

ምክክር ኮሚሽኑ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ መሠረታዊ የልዩነት ጉዳዮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የሚያስችል ታሪካዊ መድረክ ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ያለፉ የታሪክ ቁስሎችን በእውነት እና በተጠያቂነት ላይ ተመስርቶ ለማከም ትልቅ እርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች።

ይህ አዲስ ስትራቴጂያዊ የፖለቲካ አካሄድ የብሔር ማንነት እና የኢትዮጵያዊነት ዜግነት ተቃራኒ ሳይሆኑ እርስ በርስ የሚደጋገፉ ብሔራዊ አቅሞች መሆናቸውን በተጨባጭ እያሳየ ነው።

አንድ ዜጋ በቋንቋው፣ በባህሉ እና በታሪኩ ሙሉ ዕውቅና አግኝቶ ሲከበር የሀገር ባለቤትነት ስሜቱ ይጨምራል፤ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነቱም ያለው አመለካከት በዚያው ልክ ይጎለብታል።

ይህም ዴሞክራሲ የአንድ ቡድን ጊዜያዊ ድል ሳይሆን የሁሉም ዜጎች መብት የሚረጋገጥበት እና የጋራ ዋስትና የሚሆንበትን ጠንካራ ሥርዓት ይፈጥራል።

በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን እና ጥቂት አክራሪ ኃይሎች ማንነትን ብቻ በማስተጋባት የፖለቲካ ምህዳሩን የልዩነት አውድ ለማድረግ ቢሞክሩም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ለዘመናት ያቆየውን ሀገር በቀል የሽምግልና፣ የውይይት እና የእርቅ ባህል በመጠቀም የውስጥ አብሮነቱን ሲያጸና ቆይቷል።

የኢትዮጵያን መዳከም እና መበታተን ለሚመኙ ውጫዊ እንዲሁም ውስጣዊ አካላት፣ ይህ የሕዝቡ የማይበጠስ የትስስር ገመድ ሁልጊዜም የማይፈታ እንቆቅልሽ ሆኖባቸው ኖሯል።

የመደመር እሳቤ የጀመራቸው ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች እና የሌላኛውን ወገን ሀሳብ በትህትና የማዳመጥ ልምምድ፣ ኢትዮጵያ ካለፈው የታሪክ ስህተት ተምራ ወደፊት እንድትራመድ ሰፊ መንገድ ከፍተዋል።|

ኢትዮጵያ በብዝኃነቷ ላይ የተደገፈ የመግባባት ዴሞክራሲን እውን ስታደርግ የጥላቻ ፖለቲካን ሙሉ በሙሉ ትሽራለች።

በዚህም ለቀጣዩ ትውልድ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ራሷን የቻለች፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረ እንዲሁም የውስጥ ሰላሟ የተረጋገጠ ጠንካራ ሀገር ሆና መሻገር የሚያስችላትን አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ እየጻፈች ትገኛለች።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: