Search

አዲስ የትምህርት ዘመን ለኢትዮጵያ ብሩህ ዘመን ጉዞ

ማክሰኞ መስከረም 05, 2019 36

2019 አዲሱ የትምህርት ዘመን በይፋ ተጀምሯል። የትምህርት ቤት በሮች ተከፍተው ተማሪዎች ወደ መማሪያ ክፍሎቻቸው ሲገቡ፣ ይህ ጅማሬ መደበኛ የትምህርት መከፈትን ብቻ ሳይሆን፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ተረካቢ ትውልድ የመቅረጽ ከባድ ብሔራዊ ኃላፊነትን የሚያመላክት ነው።

በመሆኑም የአሁኑ መሠረታዊ ጥያቄ ትምህርት ተጀመረ ወይ? የሚለው ሳይሆን፣ በዚህ ዓመት ከትምህርት ዘርፉ ምን ይጠበቃል? የሚለው መሆን ይኖርበታል።

ከምንም በላይ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ነው። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸው ብቻውን ግብ ሊሆን አይችልም።

ይልቁንም የተማሩትን ጠለቅ ብለው በመረዳት፣ በመተንተን እና በተግባር በመፈተሽ ዕውቀትን ወደ አቅም እና ክህሎት እንዲቀይሩ ማድረግ ይገባል።

የትምህርት ሥርዓቱ ግብ ከፈተና ውጤት ባሻገር ሰፊ ትርጉም ያዘለ ነው። ተማሪዎች የያዙትን መረጃ በቃላቸው ከማስታወስ ባለፈ ፈጣሪ እና ችግር ፈቺ ሆነው እንዲወጡ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትልቅ ድርሻ አለው።

ለዚህ ስኬት ደግሞ የመምህራን፣ የወላጆች እና የትምህርት ማኅበረሰቡ የጋራ ርብርብ ወሳኝ ነው።

የፈተና ታማኝነትን ማረጋገጥ እና የኩረጃን አስተሳሰብ ከሥሩ መንቀል የግድ ሲሆን፣ ዋናው ዓላማ ዕውቀትን ለሕይወት ስኬት እና ለኢትዮጵያ ብልጽግና የሚያውል ብቁ ዜጋ መፍጠር ነው።

ትምህርት ቤቶች የዕውቀት ማዕከላት ብቻ ሳይሆኑ የዜጎች ሁለንተናዊ ስብዕና ግንባታ መሠረቶች ናቸው።

ተማሪዎች ሥነ ምግባርን፣ የዜግነት ኃላፊነትን፣ መብት እና ግዴታን፣ ብሔራዊ ጥቅምን እንዲሁም የጋራ መግባባትን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሆነው እንዲታነጹ መሥራት ያስፈልጋል።

ዛሬ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ያለው ተማሪ ነገ የሀገራችንን የልማት ጉዞ የሚመራ የዘርፉ ባለሙያ፣ ሳይንቲስት፣ ሥራ ፈጣሪ ወይም ፖለቲከኛ ነው።

በተለይም ብዝኃነት በደመቀባት ኢትዮጵያ፣ ትምህርት ቤቶች የመግባባት እና የአብሮነት ባህል ማዳበሪያ ሥፍራዎች መሆን አለባቸው።

የተለያዩ ቋንቋዎች እና ባህሎች ያሏቸው ተማሪዎች በአንድነት ሲማሩ ልዩነትን እንደ ጸጋ እና ውበት እንጂ እንደ ግጭት መንስዔ እንዳይመለከቱ ያግዛቸዋል።

ከክፍል ውስጥ ውይይቶች እስከ የጋራ ትምህርታዊ ተግባራት ያሉ ልምዶች ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት የውይይት ባህልን ያጎለብታሉ።

የዘመኑ ትምህርት ተማሪዎችን ለዲጂታሉ ዓለምና ለነገው የሥራ ገበያ በሚገባ ማዘጋጀት ይኖርበታል።

የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ሳይንስ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ሥራ ፈጠራ እና ተግባራዊ ክህሎቶች በትምህርት አሰጣጡ ውስጥ ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል።

ተማሪዎች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ፣ በቴክኖሎጂ አዳዲስ ነገሮችን የሚፈጥሩ እና የኅብረተሰቡን ችግሮች የሚፈቱ መሆን አለባቸው።

ዛሬ በስፋት የተከፈቱት የትምህርት ቤት በሮች የሚያስገቡት ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ብሩህ የነገ ተስፋ ጭምር ነው።

2019 የትምህርት ዘመንም ዕውቀት ወደ ክህሎት፣ ክህሎት ወደ ፈጠራ፣ ብዝኃነት ወደ መግባባት፣ እንዲሁም ትምህርት ወደ የላቀ ዜግነት የሚቀየርበት ውጤታማ ዓመት ሊሆን ይገባል።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: