Search

17ቱ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ለባለቤቶቻቸው ተሰጡ

ማክሰኞ መስከረም 05, 2019 31

ከኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ወጥተው ለረጅም ዓመታት በአሜሪካ የነበሩ 17 ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት ወደ ሀገር ተመልሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን በዓይነታቸው ለየት ያሉትን እነዚህን ቅርሶች ከተረከበ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ሰባት ተቋማት አስረክቧል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ሽኩር፣ የዛሬውን ርክክብ ሳይጨምር ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር ወጥተው የነበሩ 67 በላይ ቅርሶች መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ቅርሳችንን መጠበቅ ታሪካችንን መጠበቅ ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ ቅርሶች ለመጪው ትውልድ ተጠብቀው እንዲተላለፉ ባለሥልጣኑ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል፡፡

ቅርሶቹ ወደ ቀድሞ ቦታቸው መመለሳቸው የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና መንፈሳዊ ትውፊት በአግባቡ ለመጠበቅ፣ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ቅርሶቹን ለተቋማቱ ያስረከበው፣ ቅርሶቹ በባለሙያዎች እንዲጠኑ፣ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠበቁና ለምርምር ሥራዎች እንዲውሉ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

የጥንታዊ መጻሕፍት ቅርስ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም የጋራ ሀብት በመሆኑ፣ ቅርሶቹን በአግባቡ ማስተዋወቅና ለትምህርትና ለምርምር ማዋል እንደሚገባም ባለሥልጣኑ አስገንዝቧል፡፡

የዚህ ዓይነቱ የቅርስ መመለስ ተግባር፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች ለማስጠበቅና በሕገ ወጥ መንገድ የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡

በመሐሪ ዓለሙ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: