ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት እያከናወነ የሚገኘው የከተሞች ኮሪደር ልማት ሥራ ውጤት ዓለም የመሠከረለት መሆኑን ገለፁ።
ለአብነትም በቅርቡ የተመረቀውን ከእንጦጦ እስከ 4 ኪሎ የሚገኘውን ኮሪደር አንስተው፤ በዚህ ኮሪደር ከውበት እና መሠረተ ልማት ሥራዎች ባለፈ 700 አዳዲስ ቢዝነሶች እንደተከፈቱ ጠቁመዋል። ይህም በርካታ ሥራዎችን የፈጠረ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በከተሞች የመንገድ መብራቶች እና ካሜራዎች በአግባቡ በመተከላቸው ወንጀልን በከፍተኛ ደረጃ መቀንስ እንደተቻለም አንስተዋል።
በወንዝ ዳርቻ ልማትም ከሰለጠነው ዓለም የማያንስ እና ለመላው አፍሪካም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሥራ እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት። ከዚህ ባለፈ የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ቀላል የማይባሉ እንደሆኑም ነው የጠቆሙት።
ከዚህ ቀደም ከተማን ተወት አድርጎ ገጠር ላይ የማተኮር አካሄድ ተሞክሮ እምብዛም ለውጥ ያልታየበት መሆኑን አንስተው፤ አሁን ግን ከተማ እና ከተሜነትን በዝርዝር ተገንዝበን እየሰራን ነው ብለዋል።
ለዚህም የኮሪደር ልማቱን ውጤቶች ማየት በቂ መሆኑን ገልፀው፤ ከተሜነት የሰው ልጅ የብልፅግና መዳረሻ መሆኑን ጠቁመዋል።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከኮሪደር ልማቱ ምሳሌ ለመውሰድ ከመፈለግ አልፈው መጥተው እየጎበኙ ልምድ እየቀሰሙም ይገኛሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ሁላችንንም ኢትዮጵያን የሚያኮራ ነው ብለዋል።
ከተሜነት የውበት፣ የጤናማነት፣ የዘመናዊነት የአኗኗር ዘዬ መገለጫ እንደሆነም ገልፀው፤ ከተማን ያራከሰ አካሄድ የትም የማያደርስ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህ ሲባል ግን ገጠር አልተካተተም ማለት ሳይሆን ገጠርንም በኮሪደር የማልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በሰለሞን ከበደ
#EBC #ebcdotstream #PMAbiy #PMOEthiopia #Medemer #Yemedemermengist