Search

ከዐደይ አበባ ጋር የሚፈካው የተማሪዎች ብሩህ ተስፋ

ማክሰኞ መስከረም 05, 2019 90

ዘመን ዘመንን ሲተካ ዐደይ አበባ ፈክቶ አዲስ ዓመት ብሩህ ተስፋን ይዞ ይመጣል።

በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዘንድ አዲስ ዓመት እና የትምህርት ዘመን ጅማሮ አብረው የሚከሰቱ እንዲሁም በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቁ ታላላቅ ሁነቶች ናቸው።

ሀገርን ወደ ከፍታ ለማውጣትም ሆነ ትውልድን በተገቢው መንገድ ለመቅረጽ በትምህርት ዘርፍ ላይ በትኩረት መሥራት ወሳኝ እና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።

በመሆኑም የመስከረም ወር ተማሪዎች ከፍ ያለ ራዕይ ሰንቀው፣ ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ ለማሻገር ጽኑ ዓላማ በመያዝ ዳግም ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱበት ወቅት ነው።

ከአንድ የትምህርት ደረጃ ወደ ቀጣዩ ክፍል የተሸጋገሩ ተማሪዎችም ለዘመኑ ስኬት አዳዲስ ዕቅዶችን በማውጣት በርትተው ይዘጋጃሉ።

ይህን የተማሪዎችን ተስፋ ዕውን ለማድረግና የትምህርት ጥራትን አስተማማኝ በሆነ መሠረት ላይ ለመገንባት ባለፉት ዓመታት ስር ነቀል ፖሊሲዎችና መዋቅራዊ ለውጦች ተግባራዊ ተደርገዋል።

ከእነዚህም መካከል የዓለም አቀፍ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕድገትን ያገናዘበ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ፍላጎት ጋር የተጣጣመው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በዋናነት ይጠቀሳል።

በተጨማሪም ተማሪዎች በበቂ ምግብ እና በተረጋጋ አእምሮ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ታስቦ የተጀመረው የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር የተማሪዎችን የክፍል ውስጥ ተሳትፎና ውጤታማነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

ትምህርት ቤቶች ምቹ እና ማራኪ እንዲሆኑ የተሠሩት የመሠረተ ልማት ማሻሻያዎችም ለመማር ማስተማሩ ሂደት ተጨማሪ አቅም ፈጥረዋል።

በመሆኑም በዘንድሮው ዓመትም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቆ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን በደማቅ ሁኔታ በመቀበል ላይ ይገኛሉ።

አዲሱ የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ተስፋ የሚለመልምበት እና ሀገራዊ ስኬት የሚመዘገብበት እንዲሆን እንመኛለን።

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: