Search

በኢትዮጵያ የመግባባት ዴሞክራሲ ከዜሮ-ድምር ፖለቲካ ወደ ጋራ ማሸነፍ የሚያሸጋግር አዲስ ሀገራዊ ተስፋ

ማክሰኞ መስከረም 05, 2019 96

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለረጅም ዘመናት ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን ካደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የብዝሃነትን ተፈጥሮ በትክክል የሚመጥን የዴሞክራሲ ሥርዓት አለመገንባቱ ነው።

በተለይም አሸናፊው ሁሉንም የሚወስድበት የዌስትሚኒስተር አይነት የአብላጫ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ባለው ጥልቅ ብሔራዊ፣ ቋንቋዊ እና ባህላዊ ስብጥር ውስጥ ሲሞከር፣ አናሳዎችን ወይም ድምፅ የሌላቸውን ክፍሎች ከመገለል ይልቅ ወደ ፅንፈኝነትና ወደ ዜሮ-ድምር ፖለቲካ ሲገፋቸው ቆይቷል።

ኖቤል ተሸላሚው አርተር ሊዊስ እንደሚያስረዳው ብዝሃ ማንነት ባላቸው ሀገራት ውስጥ የሁሉም ድምፅ ካልተደመጠ እና አሸናፊው ሁሉንም የሚወስድበት ፖለቲካ ከልተከተሉ አደጋው የከፋ ይሆናል።

ይህንን ተግዳሮት በዘላቂነት ለመቅረፍ በፖለቲካ ሳይንቲስቱ አሬንድ ላይፕሃርት የተገነባውና በኢትዮጵያም በተግባር እየተተገበረ ያለው የመግባባት ዴሞክራሲ አዲስ ተስፋና ዘላቂ የመፍትሔ መንገድ ሆኖ ወጥቷል።

የመግባባት ዴሞክራሲ አብላጫ ቁጥር ያለው አካል ብቻ የሚያዝዝበት ሥርዓት ሳይሆን የሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ድምፅ የሚሰማበት፣ ሥልጣንና ሀብት በተመጣጣኝነት የሚካፈሉበት እና በሀገራዊ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በስምምነት የሚወሰንበት የፖለቲካ ሞዴል ነው።

ይህ ሞዴል በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ አራት መሠረታዊ አምዶች ያሉት ሲሆን፣ እነሱም የሁሉም ዋና ዋና የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች በአስፈፃሚው አካል እና በውሳኔ ሰጪ መድረኮች እንዲሳተፉ የሚያደርግ ታላቅ ጥምረት፣ አብላጫው አካል የአናሳዎችን መሠረታዊና ህልውና ነክ ጥቅሞች የሚጎዳ ውሳኔ እንዳያሳልፍ የሚከለክል የጋራ ድምፅን የመሻር መብት፣ በሕግ አውጪ፣ በካቢኔ፣ በሲቪል ሰርቪስ እና በበጀት ክፍፍል ላይ የሚታይ ተመጣጣኝነት፣ እንዲሁም ቡድኖች ለራሳቸው ብቻ በሚመለከቱ ባህላዊና ቋንቋዊ ጉዳዮች ላይ የሚያገኙት ራስን የማስተዳደር ነፃነት ናቸው።

ኢትዮጵያ የመግባባት ዴሞክራሲን ብቸኛና ዘላቂ የመፍትሔ መንገድ አድርጋ የያዘችው "እኔ ሳልሸነፍ አንተም ሳትሸነፍ በጋራ ማሸነፍ እንችላለን" በሚለው የመደመር ፍልስፍና መሠረት ማንም ዜጋ ከጠረንጴዛው ውጭ እንዳይቀር ለማድረግ ነው።

የዘመናት "ኢትዮጵያ አልሰማችኝም" የሚል የብሶትና የቁጭት ትርክትን በመስበር፣ በታሪክ አጋጣሚ ተናጋሪና ውሳኔ ሰጪ ያልነበሩ ክፍሎችን ማዕከላዊ የፖለቲካ አካል ማድረግ አስፈልጓል።

በኃይልና በጫና ከመሸናነፍ ይልቅ ልዩነቶችን በስክነትና በምክክር ወደ የጋራ አቅም በመቀየር የወል ትርክትን መፍጠር ለሀገራችን ህልውና ወሳኝ በመሆኑ የመደመር መንግሥት ይህን መንገድ መርጧል።

በኢትዮጵያ የተካሄደው ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ሂደት የመግባባት ዴሞክራሲ ከንድፈ-ሃሳብ አልፎ በተግባር መሬት የወረደበት እና ፅኑ መሠረት የያዘበት አጋጣሚ ሆኗል።

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የተደረጉ የፖለቲካ ሽግግሮች የጥቂት ልሂቃን ድራማና የይስሙላ ስምምነት በመሆናቸው ዘላቂ ሰላም ማምጣት አልቻሉም ነበር።   

ሀገራዊ ምክክሩ ግን ከመንደር እስከ ዋና ከተማ የተውጣጡ አርሶ አደሮችን፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን በቀጥታ ተሳታፊ በማድረግ የህብር ድምፆች መድረክ መሆን ችሏል።

ለምሳሌ ከደቡብ ኦሞ የካራ ማኅበረሰብ ተወካይ ሆና በምክክሩ የተሳተፈችው ሙዶ አኮ "ለብዙ ዘመናት ታሪክን ከሩቅ ቆመን እንመለከት ነበር፤ ዛሬ ግን ሀገሬ እንድናገር ጠርታኛለች" በማለት የተናገረችው ንግግር፣ የመግባባት ዴሞክራሲ ሰሚ ብቻ የነበሩትን እንዴት ተናጋሪና ባለቤት እንደሚያደርግ ህያው ማሳያ ነው።

ተሳታፊዎች ከቀረቡት አጀንዳዎች ውስጥ 99% ላይ በጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውም በውይይትና በመደማመጥ መሃል ያለውን ታላቅ የመግባባት ዴሞክራሲ አቅም ያረጋግጣል።

ይህ ሂደት ከሕገ-መንግሥታዊ ንድፍ እና ከኢፌዴሪ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የራሱ የሆነ ቁርኝት አለው። የመግባባት ዴሞክራሲን በተሟላ መልኩ ለመተግበር ሕገ-መንግሥታዊ ንድፍ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ማወጁ፣ የቋንቋዎች ዕውቅና፣ እና የፌደራሊዝም አወቃቀሩ የመግባባት ዴሞክራሲያዊ ባህሪያትን የሚያንፀባርቁ ቢሆኑም፤ ከላይፕሃርት መመሪያዎች አንጻር ሲገመገም ከተመጣጣኝ ውክልና ይልቅ የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትን መከተሉ ከሞዴሉ ያዘነበለ ነበር።

ሆኖም ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የመደመር መንግሥት የሚከተለው አካታች የፖለቲካ አቋም ይህንን የሕገ-መንግሥታዊ ንድፍ ክፍተት በተግባራዊ የፖለቲካ ባህል፣ በሀገራዊ ምክክር እና በሰፊ የምክክር መድረኮች ለመሙላት እየሰራ ይገኛል።

ወደፊትም ይህንን ልምድ ወደ ተቋማዊ አሰራር ለማሸጋገር፣ የምርጫ ሕጉን ከአብላጫ ድምፅ አሰራር ይልቅ የተመጣጣኝ ውክልናን (Proportional Representation) ወይም የተቀላቀለ የምርጫ ሥርዓትን (Mixed Electoral System) በሚያቀናጅ መልኩ ሕግ ማሻሻል ለመግባባት ዴሞክራሲው መጠናከር ወሳኝ መፍትሔ ይሆናል።

በኢትዮጵያ የመግባባት ዴሞክራሲ እውን መሆኑ የፖለቲካ ምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። ልዩነትን በግጭትና በዜሮ-ድምር ፖለቲካ ከማስተናገድ ይልቅ፣ በምክክር፣ በመደማመጥና በጋራ ባለቤትነት ማስተናገድ ከመነጠል ወደ መደመር የሚያሸጋግር የፖለቲካ ባህል ይፈጥራል።

በሀገራዊ ምክክሩ የተጣለው ፅኑ መሠረት እና የመደመር መንግሥት ያሳየው ቁርጠኝነት፣ የመግባባት ዴሞክራሲን በሰነድ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በሕግና በተቋማት ደረጃ የፀና፣ እንዲሁም በዜጎች ዕለታዊ የፖለቲካ ሕይወትና ማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ የሚኖር ሕያው ሥርዓት አድርጎታል፤ ይህም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ፖለቲካዊ መረጋጋት እና ሁሉን አቀፍ ብልጽግና መረጋገጥ ዋናው መሠረት ነው።

በሰለሞን ገዳ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: