Search

አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ዓለም አቀፍ ትብብርን የጠየቀው የኖርዲክ–አፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ነው

ማክሰኞ መስከረም 05, 2019 141

በኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ በሚገኘው የኖርዲክ አፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋም፣ የአማቂ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስና ዘላቂ የልማት አማራጮችን ለማስፋፋት አረንጓዴ ትራንስፖርትን ማሳደግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

ጉባኤው በኖርዲክ ሀገራት ማለትም በዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይና አይስላንድ እንዲሁም በአፍሪካ ሀገራት መካከል በአካባቢ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ በታዳሽ ኃይልና በዘላቂ ትራንስፖርት ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ለአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ መፍትሔዎችን ለማፍራት ያለመ ነው።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (/) የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋም አረንጓዴ ትራንስፖርትን ማስፋፋት የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ትብብርን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርንና የፋይናንስ ድጋፍን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም የአማቂ ጋዝ ልቀትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት፣ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምንና ዘላቂ የትራንስፖርት ሥርዓትን ማጠናከር እንዲሁም ከካርቦን ነፃ የኃይልና የትራንስፖርት አማራጮች ላይ የጋራ ኢንቨስትመንት ማድረግ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለአረንጓዴ ትራንስፖርት ሽግግር የሚያስፈልጉ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅሞችን ማሳደግ፣ የእውቀትና የተሞክሮ ልውውጥን ማጠናከር እንዲሁም የጋራ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ማስፋፋት የጋራ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኖርዲክ አፍሪካ ትብብር ከአካባቢ ጥበቃና ከአየር ንብረት ለውጥ ባሻገር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በዲጂታላይዜሽንና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ላይም ያተኮረ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።

በዚህም መሠረት የግል ዘርፉን በማጠናከር የጋራ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን ማበረታታት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን መገንባት በትብብሩ ውስጥ ትኩረት የሚሰጣቸው ዋና ጉዳዮች ናቸው።

በጉባኤው በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሽግግርና በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዙሪያ የፓናል ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማበረታታት የወሰደቻቸውን የፖሊሲ፣ የስትራቴጂና የስታንዳርድ እርምጃዎች እንዲሁም በኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ሽግግር ያላትን አወንታዊ ተሞክሮ ለተሳታፊዎች አጋርታለች።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: