ዓለማችን በከፍተኛ የጂኦፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሽግግር ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ደኅንነት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ሆኗል።
በዚህ ቀጣና ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የራሷ የኢኮኖሚ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ የዓለም ሀገራት የደኅንነት ማስጠበቅ ጉዳይ ጭምር መሆኑን ነባራዊ ሁኔታዎች ይመሰክራሉ።
በሕንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ላይም የቀይ ባሕር ደኅንነት በስፋት መመከሩ ደግሞ የጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ክብደት ያሳያል።
ታሪክ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ ለዘመናት የራሷ የባሕር በር ባለቤት የነበረች ታላቅ ሀገር ናት። ከጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ የንግድ ወደብ አዱሊስ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የንግድ፣ የባህል እና የሥልጣኔ መተላለፊያ ሆኖ አገልግሏል።
ሆኖም ግን፣ የኢትዮጵያን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለመገደብ በተጠነሰሰ የረጅም ጊዜ ሴራ እና ጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻ፣ ኢትዮጵያ ከባሕር በሯ እንድትገለል ተደርጓል። ይህ በሴራ የተሞላ ሒደት መቶ ሚሊዮኖችን አፍኖ በማስቀረት የኢትዮጵያን ዕድገት ከመገደቡም ባሻገር፣ ቀጣናዊ የኃይል ሚዛኑን ክፉኛ አዛብቶት ቆይቷል።
ይህ የኢትዮጵያ ከባሕር በር መገለል በሒደት ለቀጣናው እና ለዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ንግድ የደቀነው የፀጥታ ስጋት እጅግ ከፍተኛ ነው። ቀይ ባሕር ዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች በስፋት የሚተላለፉበት ቁልፍ መስመር ቢሆንም፣ ጠንካራ እና ሰላም አስከባሪ የባሕር ኃይል ያላት ኢትዮጵያ ከባሕር ዳርቻው በመገፋቷ ምክንያት ቀጣናው አስተማማኝ ጠባቂ አጥቷል።
በዚህም የተነሣ አካባቢው ለባሕር ላይ ወንበዴዎች፣ ለሽብርተኛ ቡድኖች እና ለሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪዎች ምቹ ምኅዳር ሆኗል። የኢትዮጵያ መገለል በቀይ ባሕር ላይ የደኅንነት ክፍተት እንዲፈጠር ማድረጉ በገሃድ የሚታይ እውነት ነው።
ይህንን ሐቅ በተጨባጭ ምሳሌዎች ማየት ይቻላል። የየመኑ የሁቲ ታጣቂዎች በባብ ኤል መንደብ የባሕር ሰርጥ ላይ እያደረሱ ያሉት ጥቃት እና በዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች ላይ የተደቀነው ስጋት፣ ቀጣናው ምን ያህል አስተማማኝ የፀጥታ ኃይል እንደሚያስፈልገው ያሳያል። በቅርቡ እንደ ሕንድ ያሉ ግዙፍ የኢኮኖሚ ኃይሎች በቀይ ባሕር የአፍሪካ ዳርቻ ላይ የደኅንነት አጋሮችን አጥብቀው መፈለጋቸው፣ የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ አስፈላጊነት ያጎላዋል።
ዓለም አቀፍ የባሕር ኃይሎች (የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የእስያ ኃይሎችን ጨምሮ) በሺህዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው መጥተው ቀይ ባሕርን ለመጠበቅ የሚከፍሉት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ እና ዘላቂነት የሌለው ነው።
ከሩቅ የመጡ ኃይሎች አካባቢውን በዘላቂነት ሊያረጋጉት አይችሉም፤ ምክንያቱም ጂኦግራፊያዊ ትሥሥሩ እና ቋሚው አቅም ያለው በዚሁ አካባቢ ላይ ከሚገኝ ጠንካራ ሀገር ዘንድ ብቻ ነው።
በመሆኑም፣ ኢትዮጵያ በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ ወደ ባሕር በር ተመልሳ መምጣቷ ለዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ደኅንነት ትልቅ መፍትሔ ነው።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ፣ ጠንካራ እና ዘመናዊ የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ያላት ኢትዮጵያ በባሕር ዳርቻው ላይ መገኘቷ፣ የቀይ ባሕርን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ያስችላል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ስትሆን፣ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ (እንደ ብሪክስ አባል ሀገራት እና ሌሎችም) ጋር በመተባበር የባሕር ላይ ሽብርተኝነትን እና ወንበዴነትን ለመዋጋት፣ እንዲሁም የዓለምን የንግድ መስመር ክፍት አድርጎ ለማስቀጠል ጉልህ ሚና ትጫወታለች።
ይህ ደግሞ ዓለም አቀፉ የንግድ እና የሎጂስቲክስ ሥርዓት ያለ ምንም መስተጓጎል እንዲቀጥል ያደርጋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የታሪክን ስህተት ከማረም እና ብሔራዊ ጥቅምን ከማስከበር ባለፈ፣ ለመላው ዓለም ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ ቁልፍ ምሰሶ ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር ላይ መገኘት ለሁሉም የጋራ ደኅንነት፣ ለቀጣናዊ መረጋጋት እና ለዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ብልጽግና የማይተካ ዋስትና ነው።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: