የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ በቅጠል ተራ በ4 ወራት ውስጥ የገነባቸውን 960 ቤቶች ዛሬ ለልማት ተነሺዎቹ መልሰው አስተላልፈዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት፣ የቀድሞው “ቅጠል ተራ” ለኑሮ እጅግ አስቸጋሪ፣ ለሰው ልጅ ክብር የማይመጥን፣ እጅግ የቆሸሸ፣ የተፋፈገ እና የተጨናነቀ በመሆኑ በእሳት አደጋ የነዋሪዎችን ሕይወት ጭምር አጥተናል ብለዋል።
ዛሬ ግን በስፍራው እጅግ ያማሩ፣ ዘመናዊና ሁሉም ነገር የተሟላላቸው 9 ባለ 9 ወለል ህንጻዎች ተገንብተው ሰፈሩ ወደ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ተቀይሯል ነው ያሉት።
ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው እንዳሰፈሩት፣ "የመርካቶ የበጎነት የመኖሪያ መንደር" በ11 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በተገነቡ G+8 በሆኑ 9 ብሎኮች በአጠቃላይ 960 ቤቶችን ያካተተ ነው።
በውስጡም ሰፊ የስራ እድልን የሚፈጥሩ 371 የንግድ ሱቆች፣ የህጻናት የመጫወቻ ስፍራ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ ለነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ፣ ለኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ፣ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ አለው።
ዘጠኙም ብሎኮች ላይ የጋራ መጠቀሚያ ሰገነት፣ ሊፍት፣ የፍሳሽና የኤሌክትሪክ መስመሮች ተሟልቶላቸው በዘመናዊ መልክ የተገነቡ ናቸው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: