Search

የሀረሪ ክልል ካቢኔ ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 16 አልሚዎች የመሥሪያ ቦታ እንዲሰጥ ውሳኔ አሳለፈ

እሑድ ጥቅምት 29, 2019 100

የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ከ2 ቢሊዮን 656 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ለ16 አልሚዎች በክልሉ እንዲያለሙ የመሥሪያ ቦታ በምደባ እንዲሰጥ ውሳኔ አስተላልፏል።

የመሥሪያ ቦታ እንዲሰጥ ውሳኔ የተላለፈውም በልዩ ሀገራዊ እና ክልላዊ ፋይዳ ባላቸው በተለይ በሆቴልና ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ፣ የእርሻና ምርት ማቀነባበሪያ፣ በቅይጥ አገልግሎትና በሆስፒታል እንዲሁም ለመዝናኛ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ነው።

የመሬት ምደባ የተደረገላቸው ባለሃብቶች በሚሰማሩበት የልማት መስክ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ ያላቸውና ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስለመሆናቸው ተጠቁሟል።

በአጀንዳው ጥልቅ ውይይት በማካሄድ ውሳኔውን በሙሉ ድምፅ ያጸደቀው መስተዳድር ምክር ቤቱ፣ ባለሃብቶቹ የተሰጣቸውን መሬት ለተፈለገው ልማት በማዋል በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዲገቡ አቅጣጫ አስቀምጧል።

የክልሉ መንግሥት የኢንቨስትመንት ዘርፉን የበለጠ ለማነቃቃት በትኩረት እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል።

በቀጣይም ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸውና የሕዝብን ተጠቃሚነት በሚያጎለብቱ ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በላከልን መረጃ አመላክቷል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: