ሀገር ባለውለታዎቿን ስትዘክር፣ ዛሬ ላይ በደረሰችበት መንገድ በጎ አስተዋፅኦ ያበረከቱላትን ጀግኖች ስታወሳ ትርጉሙ ብዙ ነው። አንድም የዛሬው ትውልድ በጎ አሻራውን ጥሎ እንዲያልፍ ያነሳሳል፤ ሁለትም ለሀገር ውለታ የዋለ ሁሉ ስራው እንደማይረሳ፣ ከትዝታና ከታሪክ ማህደር እንደማይፋቅም ትዕምርት ይሆናል።
ከወራት በፊት ያሉትንም ያለፉትንም የኦሊምፒክ ጀግኖች የሚዘክር ሀውልት በመዲናዋ በተገነባው አዲስ ስፖርት ፓርክ እንደተመረቀው፣ አሁን ደግሞ አንድ ግዙፍ ስብዕና በገዘፈ መንገድ ሊዘከር ጊዜው ደረሰ፣ ይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ። ይህ በአፍሪካ ስፖርት ከማለዳው ጀምሮ በጉልህ የሚታወቅና በርካታ አበርክቶዎች ያሉት ሕያው ስም ነው።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ እና ከተቀረው ዓለም ጋር የሚያስተካክላትን ግዙፍ ስታዲየም በመዲናዋ አዲስ አበባ ገንብታ እያጠናቀቀች ነው። በዚህ ግዙፍ ስታዲየም አቅራቢያ ነው ይህን አልፎ ያላለፈ፣ ርቆ ያልራቀ ባለውለታ ልትዘክረው የወደደችው።
በመደመር መንግስት እየተገነቡ ከሚገኙ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው ፕሮጀክት ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሲመረቅ፣ የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ሐውልትም አብሮ ይፋ ሆኗል። “የጂብራልታሩ ቋጥኝ“ ለኢትዮጵያ አልፎም ለአፍሪካ ስፖርት ላበረከቱት የማይዘነጋ አስተዋፅኦ ትውልድ ይዘክራቸው ዘንድ ሐውልታቸው ብግዙፉ ስታዲየም አቅራቢያ ቆሟል።
ሀገር የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት ናት። እንደ ዱላ ቅብብል የሩጫ ውድድር አንዱ ትውልድ ወደ ሌላኛው በጎውንም መጥፎውንም ያሻግራል። አዲሱ ትውልድ ደግሞ ካለፈው የተረከበውን በጎ ውርስ ይበልጥ አጎልብቶ፣ መቀረፍ የሚገባውንም አርሞ የተሻለች ሀገር ይገነባል። የመደመር እሳቤ የዚህ ነፀብራቅ ሲሆን፣ ጀግኖችን አልፈውም ሆነ በህይወት ሳሉ አሻራቸውን ያነሳል፣ ለትውልድ እንዲተላለፍ ይተጋል።
ይድነቃቸው በአካል የትናንት ቢሆኑም ዛሬ ድረስ እየተመነዘረ ያለ ሕያው አሻራ፣ ለነገም የሚተርፍ አኩሪ ውርስ ያኖሩ ባለውለታ ናቸው። ስፖርት ውድድር ብቻ ያልሆነ፣ በአሸናፈነትና ተሸናፊነት ብቻ የማይመነዘር ሚና እንዳለው በተግባር አስመስክረዋል። ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ መስራችነታቸው ጎን በፊፋ እና በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፊት ቆመው ስለ አፍሪካውያን ተከራክረዋል።
በፀረ አፓርታይድ ትግልም የማይተካ ሚና ተጫውተዋል። የነኔልሰን ማንዴላ ሀገር ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ አራማጅ ነበረችና ከዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ትታገድ ዘንድ ያለሰለሰ ጥረት አድርገዋል። በዓለም እግር ኳስ ዋንጫም የአፍሪካ ኮታ ከፍ እንዲል በብዙ ታግለዋል።
ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ተነስተው የአፍሪካን እግር ኳስ እስከመምራት የደረሱት ሰው በምድር ቆይታቸው ከሀገር አልፈው ለመላው አፍሪካ እና ጥቁር ህዝቦች የሚበጅ በጎ አሻራን ትተው አልፈዋል። አካል ቢያልፍም በጎ ስራ እንደማያረጅ፣ ከትዝታ ማኅደር እንደማይፋቅ የትውልዶችም ኩራት እንደሚሆን የገለጠ ስራ ነው፤ የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ ሐውልት።
እግር ኳስ ተጫዋቹ ይድነቃቸው፣ የስፖርት መሪው ይድነቃቸው፣ የአፍሪካ እግር ኳስ አባቱ ይድነቃቸው፣ ፓን አፍሪካኒስቱ ይድነቃቸው፣ የፀረ አፓርታይድ ታጋዩ ይድነቃቸው ስራቸው የሚያስደንቅ ስለነበር ትውልድ በስራቸው ይደነቅ ዘንድ ሀውልት ቆሞላቸዋል።
በትናንት በጎ ትዝታ ያልቆመ፣ ያልተገቡ ግብሮችን በመውቀስ ብቻ ያልተገደበ ትውልድ የራሱን አዲስ ታሪክ ይፅፋል። በመደመር እሳቤ አዲሱ ትውልድ የትናንትን በጎ ውርስ እያስቀጠለ፣ ትውልድም የራሱን በጎ አሻራ ጥሎ እንዲያልፍ መንገዱን እየጠረገ ጉዞውን ይቀጥላል፤ መዳረሻው ደግሞ ሁለንተናዊ ብልጽግና ይሆናል።
በኢትዮጵያ አልፎም በአፍሪካ እግር ኳስ ከጅምሩ አንስቶ የተኖረ በጎ ትናንት፣ በብዙ መንገድ እየተመነዘረ ያለ ዛሬ ደግሞም አሻራው ትውልድን ተጠቃሚ እያደረገ የሚቀጥል ነገ - ይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ።
በእድሪስ አሕመድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: