Search

"የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም፣ የዜጎችን ክብር የሚጠብቅ እና ተጨባጭ ውጤት የሚያመጣ ሥራ እንሠራለን" - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

እሑድ ጥቅምት 01, 2019 51

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ማጠናቀቁን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው በአንደኛው ሩብ ዓመት የከተማዋ ነዋሪዎች በአስተዳደሩ ላይ የጣሉትን እምነት እና የሰጡትን ኃላፊነት በታማኝነት ለመወጣት በተገባው ቃል መሠረት፣ በነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታና ተጠቃሚነት ላይ ለውጥ ያመጡ እንዲሁም ለቀጣይ ሥራዎች መሠረት የጣሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸው በግምገማው መረጋገጡን ገልጸዋል።

ለተመዘገበው ውጤት በከተማዋ የተፈጠረው የሥራ ትጋት፣ በታማኝነት የማገልገል ባህል፣ በመደመር መርህ በፍጥነት እና በጥራት የመፈጸም ልምድ እንዲሁም ጊዜን ሳያባክኑ ዕቅድን ወደ ተግባር የመቀየር አቅም መሆኑን ጠቁመዋል።

አክለውም፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን አደረጃጀት በማሻሻል እና ውጤትን መሠረት በማድረግ አዳዲስ የአመራር ስምሪቶች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በ90 ቀናት ዕቅዱ የክረምት በጎ ፈቃድ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የቤቶች ግንባታ እና የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን የማሻሻል ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ የቤት ችግር ያለባቸው እና በልማት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተነሱ ዜጎች ንጹሕና ክብራቸውን የሚጠብቁ ቤቶች እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ለመቀነስ የማዕድ ማጋራት ሥራዎች መከናወናቸውን እና በክረምት ግንባታ አይከናወንም የሚለውን የቆየ አስተሳሰብ በመቀየር በርካታ ፕሮጀክቶችን ማከናወን መቻሉን አስታውቀዋል።

በትራንስፖርት መሠረተ ልማት ዘርፍ አራት ትላልቅ የመኪና ማቆሚያ እና ተርሚናል ማዕከላት ወደ ሥራ መግባታቸውን፣ አዳዲስ የብስክሌት እና የእግረኛ መንገዶች፣ የውኃ ማስወገጃ እና የፍሳሽ መስመሮች በመገንባታቸው በክረምት ወቅት የሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎችን እና የሰው ሕይወት ማጣትን መቀነስ ተችሏል ብለዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትም በሰባት የገበያ ማዕከላት ሰፊ የምርት አቅርቦት እንዲገባ መደረጉን እና የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ደረጃ መሻሻሉን ገልጸዋል።

የተበታተነ አቅም ራዕይን እንደማያሳካ እና ሀገርንም እንደማይገነባ ያመለከቱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ እያንዳንዱ ሠራተኛ በግልጽ የተለየ የሥራ ድርሻ እና ተጠያቂነት ኖሮት በመደመር መርህ ተቀናጅቶ የሚሠራበትን አሠራር ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች፣  "የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም፣ የዜጎችን ክብር የሚጠብቅና ተጨባጭ ውጤት የሚያመጣ ሥራ እንሠራለን!" በማለት ከተማ አስተዳደሩ የሕዝቡ ኑሮ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

#የመደመርመንግሥት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: