የጉባ ብሥራት የሆነውን የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ የሕግ፣ የፋይናንስ እና የመሬት ዝግጅቶች ተጠናቅቀው ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት በ7ኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ነው።
ቤቶችን በፍጥነት እና በጥራት ለመገንባት የቱርኪዬ፣ የቻይና እና የኮሪያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሰፊ ጥረት መጀመሩን ጠቁመዋል።
እነዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ረጃጅም ሕንፃዎችን መገንባት የሚያስችሉ ሲሆን፣ ቤቶችን በፍጥነት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ሙከራ መጀመሩንና ወደ ሙሉ ሥራ ለማስገባት የግብአት ማስተካከያዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በመገንባት ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ የተጎበኙት ቤቶች ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በገጠርም ሆነ በከተማ በሙከራ ደረጃ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፣ ፕሮጀክቱ ከባድ ቢሆንም በእርግጠኝነት እንደሚሳካ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ከቤት ግንባታው ጎን ለጎን ቤት ፈላጊው ዜጋ ገንዘብ አግኝቶ ቤቱ ውስጥ እየኖረ የሚከፍልበትን ምቹ የፋይናንስ ሥርዓት የመዘርጋቱ ሥራ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል።
የመንገድ፣ ባቡር እና ግዙፍ መሠረተ ልማቶችን ገንብቶ የማጠናቀቅ ከፍተኛ አቅም መፈጠሩን ገልጸው፣ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ሠርቶ የመጨረስ ልምድ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: