የጎንደር ሕዝብ፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የነቁ ዜጎች በሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ቢኖራቸው እንኳ በልማት ሥራዎች ላይ አንድ ወጥ አቋም በመያዝ የመጡ የልማት ዕድሎችን በአንድነት መጠቀም እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር የመገጭ የመስኖ እና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ የመገጭ ግድብ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ አመራሮችን የሚጠቅም ሳይሆን በቀጥታ ለጎንደር እና ለአካባቢው ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ለሕዝብ የሚቆረቆር እና ለሕዝብ የሚታገል ማንኛውም አካል ይህንን ግድብ እና መሰል የልማት አውተሮችን የመጠበቅ እንጂ የማደናቀፍ ኃላፊነት ሊኖረው እንደማይገባ አስምረውበታል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ በተደረገው እንቅስቃሴ የተመረጡ የሕንፃ ቁሳቁሶችን ከሚገኙበት ቦታ ለማምጣት ከፍተኛ ዋጋ እና መሥዋዕትነት እየተከፈለ የተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎንደር ሕዝብ እና ወጣቶች ሁኔታዎችን በንቃት በመገንዘብ ጊዜን እና ዕድልን ማባከን እንደማይገባቸውም አሳስበዋል።
“በሚያጨቃጭቅ እንጨቃጨቅ፤ ልማት ላይ ግን አንድ አቋም እንያዝ፤ አንታለል፣ አንሞኝ፣ ዕድል አናባክን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የልማት ዕድሎች አንዴ ካለፉ በኋላ በርካታ ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች እንደሚበላሹ አስገንዝበዋል።
እያንዳንዱ የጎንደር ነዋሪ የመጡ የልማት አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀም እና ለቀጣዩ ትውልድ ዕድገት መሠረት መጣል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።
የሕዝብን ጥያቄ መመለስ እና ልማትን ማፋጠን ከመንግሥት የምርጫ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዘ ሳይሆን፣ ሀገርን ከማቀናት፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ሥልጣኔ ከመመለስ እና ለልጆች አስተማማኝ ነገን ከማስቀመጥ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው አብራርተዋል።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: