በአፍሪካ ቀንድ የጂኦ-ፖለቲካዊ ወጀብ ውስጥ፣ ሁኔታዎች በየጊዜው በሚለዋወጡበት እና ድንበር ተሻጋሪ ሴራዎች በሚጎነጎኑበት በዚህ ዘመን፣ አንዲትን ሀገር እንደ ቋሚ ዓለት አጽንቶ የሚያቆማት ምንድን ነው?
መልሱ በዲፕሎማሲያዊ መግለጫዎች ውስጥ ሳይሆን በጦር ግንባር ምሽጎች፣ በሰማይ ላይ በሚበርሩ የውጊያ ጀቶች እና በምድር ላይ በሚያስፈራው የሜካናይዝድ ክንድ ውስጥ ይገኛል።
አንድ ሀገር በዓለም መድረክ ላይ ቀና ብላ የምትራመደው፣ ጠንካራ ወታደራዊ አከርካሪ ሲኖራት ብቻ ነው። የኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ሕልውናም በዘፈቀደ የተገኘ ታሪካዊ አጋጣሚ ሳይሆን፣ ለ119 ዓመታት በዘመናዊ አደረጃጀት ጸንቶ በቆመው የመከላከያ ሠራዊቷ የደም፣ የላብ እና የአጥንት መሥዋዕትነት የተገነባ ሕያው ኪዳን ነው።
ከወታደራዊ ስትራቴጂ አንጻር የአንድ ጦር የመጨረሻው የውጊያ አቅም የሚለካው በታጠቀው መሣሪያ ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ ወታደሩ በውስጡ በሰነቀው የሞራል ልዕልና ነው።
ከሕዝብ አብራክ ለወጣው የኢትዮጵያ ወታደር፣ ውትድርና ለሀገር ክብር ችና ለሕዝብ ደኅንነት ሕይወትን አሳልፎ የመስጠት ቅዱስ ቃል ኪዳን ነው፤ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ” የሚለው የሠራዊቱ የዘወትር መርሕም፣ ይህ ተቋም ከኢትዮጵያ ያነሰ አንዳችም ዓላማ እንደሌለው የሚያረጋግጥ የጽናት ማኅተም ነው።
ይህ በሠራዊቱ ደም ሥር ውስጥ የሚዘዋወር የአሸናፊነት ሥነ ልቦና፣ ድንበር ተሻግሮ ዓለም ያደነቀው እና የመሰከረለት የታሪክ ሀብት ነው። በሩቅ ምሥራቅ የኮሪያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ የቃኘው ሻለቃ ሠራዊት በፖርክ ቾፕ ተራራ (Pork Chop Hill) ላይ የፈጸመው ገድል እስከዛሬ በዓለም አቀፍ ወታደራዊ አካዳሚዎች ውስጥ በአድናቆት ይወሳል።
የግሪኩ የጦር ሜዳ ዘጋቢ ቲሞን ስኮርዲሊስ በወቅቱ የኢትዮጵያን ወታደር ልዩ ዲሲፕሊን እና ጽናት ሲገልጽ የዕለት ውሏቸው “ድል እስክናደርግ ወይም እስክንሠዋ እንፋለማለን” በሚል ከብረት የጠነከረ መርሕ የተቃኘ እንደነበር እና ጥንታዊው ጀግና ሆራቲየስ በመሸጋገሪያ ድልድይ ላይ ብቻውን ተፋልሞ ጠላትን እንዳቆመው ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊው ወታደርም አንድም ምርኮኛ ሳይሰጥ እና አንዲትም ስንዝር መሬት ሳይለቅቅ ጠላትን እንደገታ በታሪክ መዝግቧል።
ይህ የፓን-አፍሪካዊነት እና የዓለም አቀፍ ሰላም ዘብነት በኮሪያ ተራሮች ብቻ አላበቃም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአፓርታይድን ቀንበር ለሰበሩ የነፃነት ታጋዮች እና መሪዎች ወታደራዊ ሥልጠና የሰጠ፣ ታንዛኒያ ነፃ በወጣች ማግስት የአየር ክልሏን በንቃት የጠበቀ፣ ለዚምባብዌ ነፃነት የታገለ እንዲሁም ከሶማሊያ እስከ ላይቤሪያ፣ ከኮንጎ እስከ ዳርፉር እና አቢዬ፣ ከደቡብ ሱዳን እስከ ሩዋንዳ እና ቡሩንዲ በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሁሉ ለአፍሪካ ወንድማማችነት እና መረጋጋት የደም ዋጋ የከፈለ የአህጉሪቱ የኩራት ዓርማ ነው።
በሀገር ውስጥም መከላከያ ሠራዊታችን የታሪካዊ ጠላቶችን የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ ባንዳዎችን እና ጽንፈኛ ቡድኖችን የሴራ መረብ እየበጣጠሰ አከርካሪያቸውን ሲሰብር፣ ድሉን የሚያጅበው በከፍተኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊን እና በሰብዓዊነት ነው።
እውነተኛ የአሸናፊነት ልዕልና የሚለካውም በጠላት ላይ በሚኖር ወታደራዊ ብልጫ ብቻ ሳይሆን፣ ከድል በኋላ የሚመጣውን ኃላፊነት በሕግ፣ በጥበብ እና በሰብዓዊነት በመወጣት ጭምር ነው። ሠራዊቱ በየግንባሩ ሕዝብ ውስጥ ገብቶ፣ የተሸበረውን አረጋግቶ፣ አካባቢውን ከጥፋት ኃይሎች እያጸዳ፣ ዜጎች ያለምንም ስጋት ወደ መደበኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ እያደረገ የሚገኘው፣ ከወገንተኝነት በጸዳ ፕሮፌሽናሊዝም እና በሕዝባዊ ወገንተኝነት የታነጸ ተቋም በመሆኑ ነው።
ይሁን እንጂ፣ የትናንት ታሪክ እና የሞራል ልዕልና ብቻውን የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ውስብስብ የደኅንነት ስጋቶችን ለመመከት በቂ አይደለም፤ ዘመኑን መዋጀት የግድ ይላል። የዛሬው የጦር አውድማ ተቀይሯል፤ ውጊያው ከመደበኛ የምድር ውጊያ አልፎ ወደ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች)፣ የሳይበር ምኅዳር እና የኤሌክትሮኒክስ ጦርነት ተሸጋግሯል።
የ130 ሚሊዮን ሕዝብ መልሕቅ የሆነችውን እና ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለችውን ኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዚህ ትርምስ በበዛበት ቀጣና ውስጥ ለማስጠበቅ፣ ብቸኛው መድኃኒት ወታደራዊ ራስን መቻል መሆኑን ተቋሙ በተግባር ተገንዝቦታል።
ትናንት በፈለግነው ልክ ኦፕሬት ለማድረግ እና ተተኳሽ ለማግኘት የነበረውን የውጭ ጥገኝነት ፈተና በመቀልበስ፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ ተአምር የሚባል የኢንዱስትሪ እመርታ ተመዝግቧል።
ከሆሚቾ የተተኳሽ መሣሪያዎች ማምረቻ እስከ ‘ስካይ ዊን’ የድሮን ኢንዱስትሪ ድረስ የተዘረጉት ግዙፍ የመከላከያ ፋብሪካዎች፣ በኢትዮጵያ ወጣቶች እና የሲቪል ኢንጂነሪንግ ምሩቃን አዕምሮ እየተመሩ የሀገርን ፍላጎት ከመሸፈን አልፈው ለውጭ ገበያ የሚተርፍ አቅም መገንባታቸው፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የምትጨርስ እና እያንሰራራች ያለች ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ክስተት ነው።
ይህ የሀገር በቀል ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ አቅም፣ ከዘመናዊ የሰው ኃይል እና የተቋም ግንባታ ጋር ተዋኅዷል። ቀደም ሲል በውስጣዊ አሠራሩ ላይ ይታዩ የነበሩ ውስንነቶችን በለውጡ ሂደት በመቅረፍ፣ ዛሬ ኢትዮጵያን የሚመጥን ሁለገብ ኃይል ተገንብቷል።
የምድር ኃይሉን ለድል የሚያበቃው እና የሠራዊቱ ቀኝ እጅ የሆነው ጠንካራው ሜካናይዝድ ኃይል፣ የአየር ክልሏን የማይደፈር ቀጣና ያደረገው ዘመናዊው የአየር ኃይል፣ የሀገራችን የጂኦ-ስትራቴጂክ ተደራሽነት የሚያረጋግጠው የባሕር ኃይል እንዲሁም የሳይበር ኮማንድን እና የሰው ኢንተለጀንስን አቀናጅቶ የሚሠራው የመረጃ መዋቅር፣ ከአካዳሚክ እና የምርምር ተቋማት ጋር ተሣሥሮ ለሲቪል ቁጥጥር የሚገዛ ዘመናዊ እና ተማሪ ተቋም እንዲሆን አስችሎታል።
የኢትዮጵያ መንገድ ሰላም፣ ልማት እና የጋራ ብልጽግና ነው፤ ዕድገታቸው እና የወደፊት ዕጣ ፋንታቸው ከኢትዮጵያ ጋር የተጋመደ ወዳጆች ሁሉ ለዚህ የሰላም ጥሪ እጃቸውን ሊዘረጉ ይገባል።
በአንጻሩ የኢትዮጵያን የሰላም እና የልማት ትኩረት እንደ ድክመት በመቁጠር፣ ከትብብር ይልቅ ትርምስን እንደ ዘላቂ ስሌት የወሰዱ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶች ወደ ገሃዱ የእውነታ ዓለም መመለስ ይኖርባቸዋል።
ሺህ ጊዜ የገጠሙንን ሺህ ጊዜ እንዳሸነፍናቸው ታሪክ ምስክር ነው፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንኳን ዛሬ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በራስ ወታደራዊ ኢንዱስትሪ ተገንብቶ፣ ትናንትም ተሸንፎ አያውቅም።
አሁን ያለበት የወትሮ ዝግጁነት እና ተቋማዊ ቁመና ለሽንፈት ቀርቶ ለሙከራም የሚያሳስብ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያን በበጎ የማይመለከቱ ኃይሎች አንዳች ክፋት እና ሴራ ከማውጠንጠናቸው በፊት ደግመው ደጋግመው ሊያሰላስሉ ይገባል።
ማሰብ ተስኗቸው ወደ ጦርነት የሚገቡ ካሉ ግን እንደተለመደው የማይረሳ እና አስተማማኝ ትምህርት የሚሰጥ የብረት ክንድ ይጠብቃቸዋል።
የ119 ዓመቱ የድል ሠራዊታችን ዛሬም እንደ ትናንቱ የማይደፈር የሉዓላዊነታችን ዋስትና ሆኖ ይቀጥላል፤ ኢትዮጵያም በጀግኖች ልጆቿ ጥረት እና መሥዋዕትነት ለዘላለም ታፍራ እና ተከብራ ትኖራለች።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: