የመገጭ የመስኖ እና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ለ19 ዓመታት ያህል በርካታ የሕዝብ እና የሀገር ሀብት እየባከነበት፣ ሕዝቡ ደግሞ በውኃ ጥም እየተቸገረ ሳይጠናቀቅ መቆየቱ እርግማን የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገ አጣዳፊ እና የተቀናጀ እንቅስቃሴ ወደ ታላቅ በረከት መለወጡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር ከተማ ተገኝተው የመገጭ ፕሮጀክትን በይፋ ሲመርቁ ባደረጉት ንግግር፣ ፕሮጀክቱን በአካል ያዩት የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የጎርጎራን ፕሮጀክት ለማስመርቅ በመጡበት ወቅት እንደነበር አውስተዋል።
በወቅቱ የጎንደር ወዳጆቻቸው በከተማዋ ውስጥ “እርግማን የሆነ ፕሮጀክት አለ፤ ወይም ይጥፋ ወይም ወደ በረከት ይቀየር” የሚል ጥያቄ አቅርበውላቸው እንደነበር እና ከጎርጎራ ቀጥታ ወደ ቦታው መጥተው ሲያዩት አጠቃላይ አያያዙ በባለቤት የተያዘ አይመስልም ነበር ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው የፕሮጀክቱን መጓተትና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችን አስመልክተው ሰፋ አድርገው ያበራሯቸው ዋና ዋና ነጥቦች፦
የ19 ዓመታት መጓተት የበደልና የጥፋት ስብራት፦ አንድ ፕሮጀክት 19 ዓመት ሙሉ ብዙ ገንዘብ እየባከነበት እና ሕዝቡ በውኃ ጥም እየተቸገረ አለመጠናቀቁ በእውነትም እርግማን፣ በደል፣ ግፍ እና ክፉ አሰራር እንደነበር ገልጸዋል።
19 ዓመት ማለት ያኔ የተወለደ ሰው ዛሬ እዚያ ቦታ ተቀጥሮ ሊሰራ የሚችልበት ረጅም ጊዜ በመሆኑ፣ በማንኛውም ደረጃ ያለ አካል አለመጀመር ወይም የማይቻል ከሆነ “አልችልም” ማለት እንጂ እችላለሁ ብሎ ቃል ከገባ በኋላ አንድ ሰው ተወልዶ ዩኒቨርስቲ እስኪገባ ድረስ ፕሮጀክት ማዘግየት የከፋ ጥፋት መሆኑን አስምረውበታል።
የተወሰዱ አጣዳፊ የመፍትሔ እርምጃዎች፦ ያንን እርግማን ነቅሎ ወደ በረከት ለመቀየር የተደረገው ሥራ የበጀት ድጋፍ ማድረግ ብቻ እንዳልነበረ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የነበረውን ኮንትራክተር በመቀየር፣ ቀድሞ የተሠራ እና ለጎንደርም ሆነ ለግድቡ የማይመጥነውን ሥራ በማፍረስ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ ፕሮጀክቱ በባለቤትነት ስሜት ተጠናቆ ዛሬ ለምርቃት እንዲበቃ መደረጉን አብራርተዋል።
ከጀመሩ መጨረስ እና የሕዝብን ጥያቄ መመለስ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው ድንጋይ እንደ ዘር እየዘሩ የማያበቅል፣ የማያልቅ እና የማይከወን የማድረግ ልምምድ የነበረው ሀገራችን ያላትን እምቅ አቅም ወደ ድርጅታዊ አቅም የመቀየር ልምዷ ውስን በመሆኑ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ውኃው እምቅ አቅም ሆኖ እያለ የጎንደር ሕዝብ ሲጠማ እና አርሶ አደሩ ማረስ ሳይችል መቆየቱን በማንሳት፣ የዜጎችን ሕይወት በተጨባጭ ለመቀየር ድርጅታዊ አቅም የሆነውን ግድብ መገንባት እንደተቻለ እና አሁንም ከጀመሩ መጨረስ እና የሕዝብን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎንደር የሚገባት እንዲህ ያለው አዎንታዊ የልማት ሥራ መሆኑን በመጠቆም፣ “የገባነውን ቃል እንፈጽማለን፤ ከጀመርን እንጨርሳለን፤” ብለዋል። ይህም ከምርጫ ጋር ሳይሆን ሀገር ከመገንባት እና የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ከመፍጠር ጋር በቀጥታ የተቆራኘ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: