ለአስራ ዘጠኝ ዓመታት ያህል ተጓትቶ የቆየውና በአማራ ክልል በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው የመገጭ የመስኖ እና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገ ልዩ የአመራር ክትትልና ርብርብ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በዚሁ ጊዜ ፕሮጀክቱ ላለፉት 19 ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ሲንቀራፈፍ እና ሲንከባለል የቆየ ሲሆን የመደመር መንግስት ያደሩ ፕሮጀክቶችን ባልሰሩባቸው ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ማሳበብ ሳይሆን እዳዎችን በፍጥነት የማረም እና የማስተካከል ዋነኛ ማሳያ አድርገን እንወስደዋለን ብለዋል።
ከ185 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ይህ ፕሮጀክት፣ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ25 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል አቶ አረጋ ።
ፕሮጀክቱ በጎንደር ዙሪያ፣ በደንቢያ ወረዳና በጎንደር ከተማ የገጠር ቀበሌዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን ኑሮ ከማሻሻሉም ባሻገር፣ የጎንደር ከተማን የዘመናት የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት እንደሚያቃልል፣ ለዓሣ ሀብት ልማትና ለቱሪዝም መስህብነት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር እንዲሁም የአካባቢውን የአየር ንብረት በማስተካከል ረገድ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።
በአካባቢው በፌዴራል መንግስት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች የመደመር መርሆዎችን በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የፋሲለደስ ቤተ-መንግስት እድሳት ታሪክን የማደስ፣ የጎርጎራ ፕሮጀክት ደግሞ የተፈጥሮ ጸጋን በዘላቂነት የማልማት አቅጣጫ ማሳያዎች መሆናቸውን አውስተዋል።
ጎን ለጎንም በልማት ሂደት ውስጥ በበቂ ሁኔታ ተጠቃሚ ያልነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አማካኝነት በጎንደር ከተማ እየተገነቡ ያሉት የሴቶች የኑሮ ማቅለያ ፕሮጀክት እና ማየት ለተሳናቸው ዜጎች የሚገነባው የመማር ማስተማር ማዕከል የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጫዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ መገጭ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ባለፉት ሁለት ዓመታት ሌት ተቀን ተሰርቶ ለፍጻሜ እንዲበቃ በጀት በመመደብና የቅርብ አመራር በመስጠት ላስተባበሩት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ለፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር አብርሃም በላይ ምስጋና አቅርበዋል።
በረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: