Search

የኢትዮጵያ ወደ ባሕር በር መድረስ ለቀጣናው ሰላም እና ለጋራ ዕድገት መሠረት ይሆናል፦ ምሁራን

ዓርብ ጥቅምት 13, 2019 61

የኢትዮጵያ ወደ ባሕር በር የመድረስ መብት በውጭ ኃይሎች ሰነድ እና ውሳኔ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ ከሀገራችን የረጅም ዘመን ታሪክ፣ ሥነ ሕዝብ እና ጂኦግራፊያዊ እውነታ ጋር በጥብቅ የተሣሠረ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ማንነቷ እንደሆነ ምሁራን ገለጹ።

ከኢቲቪ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረ ማርያም እና የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር እና ለሕንድ ውቅያኖስ በነበራት ተፈጥሯዊ ትሥሥር ምክንያት የሚነሣውን የባሕር በር ፍላጎት እንደ ቀጣናዊ ስጋት አድርጎ ማስቀመጥ፣ ሀገራችንን ከታሪካዊ እና ሥነ ልቦናዊ ማንነቷ የመነጠል ታሪካዊ ሴራ ነው።

አካሄዱ ኢትዮጵያ በጂኦ-ፖለቲካው መድረክ እንዳትበለጽግና ዘላቂ ሰላም እንዳታገኝ የተሸረበ ጠንቀኛ መንገድ እንደሆነም አብራርተዋል።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌር ዓለማየሁ ገብረ ማሪያም እንደሚያስረዱት፣ የቀጣናው አለመረጋጋት በዋናነት በቀጥታ እና በእጅ አዙር በሚሠሩ ኃይሎች መሆኑን ተናግረዋል።

“ግብጽ እና ኤርትራ በእጅ አዙር እና በተለያዩ አቀራረቦች ቀጣናውን በማንወራጨት እና የኢትዮጵያን መረጋጋት በማናጋት ረገድ የሚጠቀሱ ናቸው” የሚሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፣ ኢትዮጵያ እያሳየች ያለችው ግዙፍነት እና ፈጣን ዕድገት ለእነዚህ አካላት ስጋት ሆኖ መታየቱን ይገልጻሉ።

አክለውም የምዕራቡ ዓለምም ሆነ አሜሪካ ኢትዮጵያ የቀጣናው ሠረታዊ የሰላም ማዕከል መሆኗን እንደሚረዱ እና ያለ ኢትዮጵያ ሚና በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ እንደማይችል የተረጋገጠ እውነታ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።

የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት፣ ኢትዮጵያ በአካባቢው ካሉ ሀገራት ጋር ስትነጻጸር ትልቅ የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ አቅም ያላት ኃያል ሀገር ነች።

የኢትዮጵያ ወደ ባሕር ዳርቻ መውጣት በቀይ ባሕር፣ በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በባብ ኤል-መንደብ ያለውን ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ሰላም ከማስከበር አንጻር ትልቅ ሚና አለው ብለዋል። አካባቢው ላይ የሚታዩ የአሸባሪ ቡድኖችን ጫና ለማክሸፍ እና ሰላም ለማስፈን ኢትዮጵያ የምታደርገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለመሆኑም ነው የገለጹት።

የባሕር በር ማግኘት ከወደብ አገልግሎት ባሻገር ሰፊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ስለሚፈጥር እንደ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ሶማሊላንድ ያሉ ጎረቤቶችን በጋራ የሚያበለጽግ እና የኢኮኖሚ ትሥሥርን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ማንንም ሀገር ለጦርነት የመተንኮስ ወይም የሌሎችን ሉዓላዊነት የመጋፋት ዓላማ እንደሌለው፣ ይልቁንም በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሕዝብ ቁጥርን እና የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚመጥን የሕልውና፣ የፍትሕ እና የልማት ጥያቄ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ያመላክታሉ።

ቀደም ሲል በዓለም ላይ ከሚታወቁ ታላላቅ ኃያላን መንግሥታት አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ የባሕር በሯ የተዘጋበት መንገድ አሳዛኝ እና የዓለም አቀፍ ተሰሚነቷን እና ዲፕሎማሲዋን ያቆሰለ ነበር።

ስለዚህ የባሕር በርን መልሶ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት መሠረተ ልማትን ከማግኘት ባለፈ ታሪካዊ ቁስልን የሚያድን፣ ሙሉ ማንነትን የሚያጎናጽፍ እና የሀገራችንን ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ወደነበረበት ከፍ የሚያደርግ ነው።

ኢትዮጵያ በባሕር በር ዙሪያ የምታነሣው ሰላማዊ ጥያቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ በባለብዙ ወገን መድረኮች እና በብሪክስ አባል ሀገራት ዘንድ ድጋፍ እና አዎንታዊ ምላሽ እያገኘ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሕልውና እና ብልፅግና ከዓባይ ወንዝ እና ከቀይ ባሕር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ቢሆንም፣ ቀደም ሲል ስለ ጉዳዩ መነጋገር እንደ ነውር ይቆጠር እንደነበር ይታወሳል።

ሆኖም የመደመር መንግሥት የባሕር በር ጉዳይን የዕለት ተዕለት ብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ፣ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ላይ የሚገባውን ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል።

አሁን ላይ የባሕር በር ጥያቄ የሕልውና፣ የፍትሕ እና የታሪክ እውነታን የመመለስ ጉዳይ ሆኖ በመደመር ሂደት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: