Search

“ሀገራዊ የልማት ውጥኖችን ወደ ውጤት እንዳንቀይር ያሰሩን ሦስት ዋና ዋና ስብራቶች ሊቃኑ ይገባል”፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ዓርብ ጥቅምት 13, 2019 61

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ወደ ድርጅታዊ እና ተጨባጭ አቅም በመቀየር የዜጎችን ሕይወት በተጨባጭ ለመለወጥ የሚደረገውን የልማት ጉዞ ያደናቀፉ ሦስት ዋና ዋና ሀገራዊ ስብራቶች ሊቃኑ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር ከተማ የመገጭ የመስኖ እና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደተናገሩት፣ ሀገራችን በርካታ የተፈጥሮ ሀብት እና እምቅ አቅም ያላት ቢሆንም፣ ይህንን አቅም ወደ ድርጅታዊ አቅም እና ወደ ተጨባጭ ውጤት የመቀየር ልምምዷ ውስን በመሆኑ ፕሮጀክቶች ለረጅም ዓመታት ሳይጠናቀቁ ይቆያሉ።

የመገጭ ውኃ እምቅ አቅም ሆኖ እያለ የጎንደር ሕዝብ ሲጠማ እና አርሶ አደሩ ማረስ ሳይችል የቆየው ግድቡን የመገንባት ድርጅታዊ አቅም ባለመፈጠሩ እንደነበር ገልጸው፣ የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር እና ፕሮጀክቶችን በውጤት ለማጠናቀቅ ሦስት እጅ ተወርች ያሰሩን ስብራቶች ሊቃኑ እንደሚገባ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመገጭ ፕሮጀክት ለ19 ዓመታት ያህል መጓተቱን መነሻ በማድረግ ሰፋ አድርገው ያበራሯቸው ሦስቱ ሀገራዊ ስብራቶች፦

1ኛ) ሉዓላዊ አቅም አለመደርጀት፦ ፕሮጀክቶችን ስንጀምር፣ ስናቅድ እና ስናስብ ባለን ሀብት፣ የሰው ኃይል እና ኮንትራክተር 90 በመቶውን ሠርተን የቀረውን 10 በመቶው ሌላ የውጭ አካል ስንጠብቅ ያ አካል አንቆ ሥራውን ያቆመዋል።

ኢትዮጵያ ባላት አቅም ጀምራ ማጠናቀቅ እንዳለባት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በራሳችን ልጆች አቅደን፣ በራሳችን ፍላጎት እና መሻት ተግብረን በራሳችን አቅም የምንጨርስበትን ሉዓላዊ አቅም መገንባት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

2ኛ) ጨርሶ አለመጀመር እና ከውኖ አለመጨረስ፦ አንድን የልማት ሥራ ለመሥራት እና ለመለወጥ ስንነሣ በአእምሯችን ውስጥ ጨርሰን አንጀምርም። ገና ስንጀምር ዲዛይኑም፣ ሐሳቡም፣ ሠራተኛውም እንደ አዲስ የሚጀመር በመሆኑ እና በአዕምሯችን ጨርሰን ስለማንጀምር አንድን ሥራ ተከታትሎ ለፍሬ የማብቃት ልምምዳችን አናሳ ነው።

በየቦታው ድንጋይ እንደ ዘር እየዘሩ የማያበቅል እና የማይከወን የማድረግ ክፉ ልምምድ መቀየር እንዳለበት አመልክተዋል።

3ኛ) ሥርዓታዊ ሥልጡንነት ማነስ፦ በታላቁ የመደመር ስትራቴጂ እንደተቀመጠው በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት መካከል የመናበብ፣ የመተሣሠር እና በጋራ የመሥራት ሥልጡንነት ማነስ ሌላው ማነቆ ነው።

ይህንን የመገጭ ሥራ ፌዴራል ወይም ክልል ብቻቸውን ሊሠሩት እንደማይችሉ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተናብበን በጋራ መቆም በሚገባን ቦታ ላይ የመናበብ ክፍተት ሲኖር ፕሮጀክቶች ተጀምረው እንደማይጠናቀቁ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ጎንደር ገና ያልተነካች፣ የሚገባትን ያጣች እና ገና ብዙ ልማት የሚገባት ጥንታዊ እና ድንቅ ከተማ መሆኗን ጠቅሰው፣ “የተሠራው ሥራ በጣም ትንሽ በመሆኑ በዚህ የሚቆም እርካታ ሊኖረን አይገባም” ብለዋል።

ሕዝቡም በትንሽ ነገር ረክቶ ድህነትን ለዘመናት ከመሸከም ይልቅ፣ ይበልጥ እንድንሠራ እና እንድንተጋ ጥያቄ እያቀረበ ከመንግሥት ጎን በመቆም አብሮ ማልማት እንዳለበት አደራ ብለዋል።

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: