Search

“የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ለእኛም ተነሣሽነትን ፈጥሮልናል”፦ የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ

ዓርብ ጥቅምት 13, 2019 63

በጎንደር ከተማ የተገነባው የመገጭ የመስኖ እና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት መጠናቀቅ፣ በሀገራቸው ተጀምሮ የተቋረጠውን ተመሳሳይ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ዳግም ለማስጀመር ትልቅ መነሣሣት እንደፈጠረባቸው የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ አስታወቁ።

ፕሬዚዳንት ማሃማ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በመሆን ታሪካዊቷን የጎንደር ከተማ በጎበኙበት እና የመገጭ ፕሮጀክትን በይፋ ባስመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአመራር ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

በ1999 ዓ.ም የተጀመረው የመገጭ ፕሮጀክት ለዓመታት ተጓትቶ ከቆየ በኋላ፣ ከሦስት ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አነሣሽነት አዲስ ሕይወት ዘርቶ ለምረቃ መብቃቱን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

ይህም በጋና ለዓመታት ተጀምሮ የቆየውን የ‘ፕዋሉጉ’ የመስኖ እና የኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ እንዲያስጀምሩ እንዳነሣሣቸው ገልጸዋል።

“በእርግጥም ይህ ሥነ ሥርዓት አነሣሥቶኛል፤ ምክንያቱም በጋና ከብዙ ዓመታት በፊት የተጀመረ ነገር ግን የተተወ ተመሳሳይ ግድብ አለን። ስለዚህ ይህ ፕሮጀክት ወደ ሀገሬ ተመልሼ የ‘ፕዋሉጉ’ የመስኖ ፕሮጀክትን እንደገና እንድቀሰቅስ እና እንዳስጀምር ያነሣሣኛል” ሲሉ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ዋነኛ ፋይዳ ልክ ይህ የመገጭ ፕሮጀክት እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ወደ 25 ሺህ ሔክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ በማልማት ለጋና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጡ እንደሆነም ፕሬዚዳንት ማሃማ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የኢትዮጵያ እና የጋናን ታሪካዊ ትሥሥርም አውስተዋል። ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን እና ጋናም ከሰሐራ በታች ካሉ ሀገራት ነፃነቷን በማወጅ ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሰዋል።

በተለይም የጎንደር ስም በጋና ልዩ ቦታ እንዳለው ሲገልጹ፣ በሀገራቸው ዋና ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ‘ጎንደር ባራክስ’ (የጎንደር የጦር ሰፈር) የሚባል ስፍራ መኖሩን እና ይህም በታኅሣሥ 31ዱ የጋና አብዮት ወቅት ዋና መምሪያ እንደነበር አብራርተዋል።

የቀደሙት የአፍሪካ መሪዎች አህጉሪቱን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት መታገላቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ማሃማ፣ የዛሬዎቹ መሪዎች ዋነኛ ኃላፊነት ደግሞ ለሕዝባቸው ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን እና ብልጽግናን ማምጣት መሆኑን አስምረውበታል።

በበረከት ሽመልስ

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: