351 ሔክታር አጠቃላይ ስፋት እና የ10 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን–ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት ተጠናቆ በይፋ መመረቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋዊ መልእክታቸው እንደገለጹት፤ ይህ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ዘመናዊ፣ አረንጓዴ እና ሁሉንም አካታች የሆነች አዲስ አበባን የመገንባት ሀገራዊ ራዕይን እውን የሚያደርግ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቱ ያካተታቸው ዋና ዋና የመሠረተ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ አቅሞች፦
• ለኑሮ ተስማሚ የከተማ ከባቢ፦ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶችን፣ የተቀናጁ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎችን፣ ፕላዛዎችን፣ አምፊ ቲያትሮችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን እና የውኃ ትርዒት ማሳያዎችን ያካተተ ነው።
• ዘመናዊ የትራንስፖርት እና የኃይል አቅርቦት፦ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችን እንዲሁም ከ100 በላይ መኪኖችን በአንድ ጊዜ መሙላት የሚያስችሉ ስምንት የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ማዕከላትን የያዘ ነው።
• የአካባቢ ጥበቃ እና የወንዝ አስተዳደር፦ በወንዝ አስተዳደር፣ በአፈር እና ውኃ ጥበቃ እንዲሁም በወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ስፍራዎች አማካኝነት የአካባቢ ጥበቃን ከከተማ ገጽታ ለውጥ ጋር ማቀናጀት ተችሏል።
• የኢኮኖሚ ዕድሎች እና የገበያ ማዕከላት፦ ቀደም ሲል በወንዝ ዳርቻው አካባቢ ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች የዕደ-ጥበብ ምርቶችን እንዲያመርቱ እና እንዲሸጡ የሚያስችል የገበያ ማዕከል እንዲሁም የግብርና አምራቾችን ከገበያው ጋር የሚያገናኝ የግብርና ምርት መሸጫ ማዕከል ተዘጋጅቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የእኛ ራዕይ ለዛሬው እና ለሚቀጥሉት ትውልዶች ውብ ብቻ ሳትሆን ምርታማ፣ ሁሉንም አካታች እና ሕዝቧን የምትመጥን ከተማ መገንባት ነው” በማለት የመደመር መንግሥትን ጽኑ አቋም ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: