የኢትዮጵያ የዘመናት ሉዓላዊነት፣ የጽናት ገደብ እና የታሪክ ዓርማ የሆነው ጀግናው የኢትዮጵያ ወታደር፣ የቤተሰቡን ፍቅር፣ የሞቀ መኖሪያውን እና የግል ምቾቱን ወደ ጎን ትቶ “ሀገር ከሁሉ በፊት” የሚለውን መርሕ በደሙ የሚጽፍ ሀገር ወዳድ ነው።
የኢትዮጵያ ወታደር፣ ከውጭ የሚመጣውን ወራሪንም ሆነ የሀገርን ሕልውና ለመሸርሸር የሚዶልተውን የውስጥ ባንዳ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚመክት፣ የሀገርን ሰላም እና የዜጎችን እፎይታ ለማረጋገጥ ቀን ከሌሊት በጽናት የሚቆም የሕዝብ ተስፋ እና አለኝታ ነው።
በየትኛውም የፈተና ማዕበል ውስጥ አልፎ ደሙን፣ ላቡን እና ሕይወቱን ለእናት ሀገሩ መሥዋዕት የሚያደርገው ሠራዊታችን፣ የኢትዮጵያ የማይደፈር አጥር፣ የወገን ኩራት እና የዘላቂ ሰላም ባለቤት ነው።
ከሠራዊቱ መለዮ ጀርባ የሚታየው ለእናት ሀገሩ በጽኑ የሚያስበው፣ የሚመታው እና የሚሠዋው ያ እውነተኛ የልብ ምት ነው። የመከላከያ ሠራዊት አባል ማለት ከቤቱ ሲርቅ የእናቱን ፍቅር፣ የአባቱን አርቆ አሳቢ ምክር፣ የባለቤቱን ስስ ናፍቆት እና የልጆቹን ሞቃት እቅፍ በልቡ ታቅፎ የሚጓዝ የሕይወት ታሪክ ባለቤት ነው።
በስልክ መስመር የሚሰማው የልጁ የየዋህነት ድምፅ የድካሙ ማረፊያ፣ ከቤተሰቡ የሚደርሰው መልዕክት ደግሞ በፈተናዎች መካከል የሚያበረታታው እና የነገን ብሩህ ተስፋ የሚያሳይ ስንቁ ነው።
ሀገሩ ስትጠራው ሁሉንም የግል ፍላጎት እና ምቾት ወደ ጎን አድርጎ የተሰጠውን ታሪካዊ ተልዕኮ ለመወጣት በቁርጠኝነት ይሰለፋል። በዓላትን ከቤተሰቡ ጋር ሳይሆን በበርሃ እና በግንባር ያሳልፋል፤ በደስታ እና በኀዘን ቀናት ከሚወዳቸው ወዳጆቹ ሊርቅ ይችላል።
ይህ ግን ቤተሰቡን እና ዘመዶቹን ስለማይወድ ሳይሆን፣ ከምንም በላይ የሚወዳት እናት ሀገሩ እና ሕዝቧ በሰላም፣ በክብር እና በነፃነት እንዲኖሩ ካለው ጥልቅ፣ መለኪያ ከሌለው የሀገር ፍቅር የሚመነጭ ነው።
በየግንባሩ በሚጋረጡ ፈተናዎች መካከል የሚያልፈው ይህ ጀግና፤ የራሱን የግል ሕልሞች እንደያዘ የሀገሩን ደኅንነት እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሌሊት እና ቀን ይተጋል።
119ኛው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን የዚህን ታላቅ ኃላፊነት የምናስታውስበት፣ የወታደሩን የማይተካ መሥዋዕትነት የምናከብርበት እና ለሀገር ሰላም የሚደረገውን የተጋድሎ ጉዞ በኩራት የምንዘክርበት ልዩ ሀገራዊ ቀን ነው።
ከመለዮው ጀርባ ያለውን ሰው ስናስብ፣ የምናየው የጦር ልብስ የለበሰ ወታደርን ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገሩ ሕልውና ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት የቆመ አባትን፣ እናትን፣ ልጅን፣ ወንድምን እና ባልን ነው።
ለእናት ሀገሩ ሲል ከቤተሰቡ የሚርቀው፣ የራሱን ደስታ እና ሕይወት ለሌሎች ሰላም አሳልፎ የሚሰጠው ወታደር የሀገራችን የቁርጥ ቀን ኩራት ነው።
ለጀግንነቱ፣ ለላቀ ቁርጠኝነቱ እና ለሚከፍለው የሕይወት መሥዋዕትነት ሁልጊዜም ላቅ ያለ ሀገራዊ ክብር እና ሞገስ ይገባዋል።
እንኳን ለ119ኛው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን በሰላም አደረሳችሁ!
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: