Search

12ኛው ጣና ፎረም በአህጉራችን በሚገጥሙን ተግዳሮቶች ዙሪያ በግልጽ እንድንወያይ ዕድል ፈጥሯል፦ የጋናው ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ

እሑድ ጥቅምት 15, 2019 63

"በአፍሪካ ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት እና ጂኦፖለቲካዊ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው 12ኛው የጣና ፎረም ተጠናቅቋል።

የጋናው ፕሬዚዳንት እና የጣና ፎረም ቦርድ ሰብሳቢ ጆን ድራማኒ ማሃማ በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ 12ኛው የጣና ፎረም በአፍሪካ ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶችን ለመወያየት ከቀዳሚዎቹ መድረኮች አንዱ ሆኗል ብለዋል።

ባለፉት ሦስት ቀናት አህጉራችን አፍሪካ ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ጥልቅ ውይይቶችን ማድረጋቸውን እና ሂደቱም ስኬታማ እንደነበር ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

ጣና ፎረም የአፍሪካን የሰላምና ደኅንነት ሁኔታ እንዲሁም በአህጉራችን የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች በግልጽነት የመተንተንና የመወያየት ዕድል ሰጥቶናል ብለዋል።

በፎረሙ ውይይቶቹ ግልጽ፣ ጥልቅ እና በአስተዋይነት የተመሩ እንደነበሩም አመላክተዋል። የውይይት ውጤቶችን ወስደን በጥልቀት በመመርመር አፍሪካን እያናወጡ ለሚገኙት በርካታ ግጭቶች መፍትሔ ለማፈላለግ ጠቃሚ መሣሪያ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

“አሁን ግን እዚህ የተወያየንባቸውን ጉዳዮች ለመፍታት ቁርጠኛ ሆነን ከዚህ መውጣት ይኖርብናል” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

መነጋገር እና መወያየት ጥሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህ የበለጠ ጠቃሚው ግን ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ስለሆነ ከውይይት ወደ ተግባር መሸጋገር እንዳለብን ጠቁመዋል።

ዛሬ ከዚህ መድረክ ልንወስደው የሚገባው አንዱ ጉዳይ የአፍሪካ አንድነት እና መተባበር ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ነው ሲሉም አስምረውበታል።

ለፎረሙ ስኬታማነት ኢትዮጵያ ላደረገችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: