የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በ119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን ለመከላከያ ሠራዊቱ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ዜጎች ዕውቅና ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ የመከላከያ ሠራዊትን እናፈርሳለን የሚሉ ደፋር ባንዳዎች እንዳልነበሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በዚህ ዘመናዊ የዲጂታል ዘመን የመከላከያ ሠራዊትን ለማፍረስ እና ከሕግ ውጪ ስልጣን ለመያዝ የሚሞክሩ አካላት መፈልፈላቸውን የጠቆሙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ እነዚህ አካላት የኢትዮጵያን ምሶሶ አፍርሰው ሀገር ለማፍረስ የሚከጅሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አክለውም በዚሁ ዓመት መስከረም 13 ቀን ከግብፅ እስከ ካርቱም እና አስመራ የተሸረበውን ሤራ የተቀበለውና መላላክ የተጠናወተው ህወሓት በሰሜን ወሎ፣ በዋግ እና በአፋር ግንባሮች ጦርነት ቢከፍትም፣ ራሱ በከፈተው ጦርነት እንዳልነበረ መሆኑን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በምፅዋ ወደብ በኩል የተላለፈላቸውንና የአንድ መካከለኛ ሀገር መከላከያ ትጥቅ ሊሆን የሚችል የጦር መሣሪያ ሠራዊቱ መቆጣጠሩን በመግለጽ የጠላቶች ዱለታ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል።
መከላከያ ሠራዊት ተዳክሟል በሚል የተሳሳተ ግምገማ የተነኮሱ አካላት ለመከላከያ የተመኙትን መፈራረስ እራሳቸው ተጎንጭተው የትግራይን ንብረት ጭነው ወደ መንደፈራ መግባታቸውን አንስተዋል።
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፤ ህወሓት ባለፉት ስምንት ዓመታት የከፈታቸውን አራት ጦርነቶች በሙሉ ተሸንፎ ሳለ፣ ሽንፈቱን ላለመቀበል እና በፕሮፓጋንዳ ለመሸፈን "ስልታዊ ማፈግፈግ አደረግን" የሚል ምክንያት እንዳቀረበ ገልፀዋል።
በዚህም የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮችን በመጥቀስ ህልውና በሚል የሚቀርቡት ሀሳቦች ዋናውን ጠላት ለመጠበቅ የተጣበቁ መርዞች መሆናቸውንና ይህንን መርዝ ተሸክሞ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ አደጋ የደቀነው የሀገር ውስጥ ባንዳ መሆኑን አስረድተዋል።
ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያን ማንሰራራት እንደ ህልውና አደጋ በመቁጠር ሲወጋንና ሲያዋጋን የኖረው ታሪካዊ ጠላት፣ ዛሬም በብሔሮች ህልውና ሽፋን ተሸሽጎ እኩይ ዓላማውን ለማስፈጸም እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: