Search

ከአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከልነት ወደ አረንጓዴ መዲና፦ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት እና የCOP32 ታሪካዊ ዝግጅት

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 84

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን በመቋቋም ረገድ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ሀገራት አንዷ ናት።

ሀገራችን 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ የምታደርገው ጥልቅ ዝግጅት የዚህ ታላቅ ሀገራዊ ቁርጠኝነት ትልቁ ማሳያ ሆኖ ይወሰዳል።

በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የመዲናዋ አዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ነው።

ለዓመታት የአዲስ አበባ ወንዞች እና የወንዝ ዳርቻዎች የኢንዱስትሪና የቤት ውስጥ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ መጣያ በመሆናቸው ተፈጥሯዊ ሥነ ምኅዳራቸው ተጎድቶ ቆይቷል።

የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቱ ይህንን ታሪክ በመቀየር በወንዝ ዳርቻዎች ላይ የተደረጉ የጽዳት፣ የዛፍ ተከላ እና የውኃ ፍሰት ማስተካከያ ሥራዎች የወንዞችን የተፈጥሮ ፍሰት በመመለስ የብዝኃ ሕይወት መጠለያ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሀገር በቀል ዛፎች እና አረንጓዴ ተክሎች በወንዞች ዳርቻ መተከላቸው የከተማዋን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ስበት አቅም በመጨመር አየርን የማጽዳት ሚና ተጫውተዋል።

በተጨማሪም አረንጓዴ ስፋቶችን በመጨመር እና የውኃ አካላትን በማልማት በከተማዋ ውስጥ የሚፈጠረውን ከፍተኛ የሙቀት መጠን መቀነስ ተችሏል። ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎች አዲስ የሕይወት ዘይቤና የኢኮኖሚ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል።

ፕሮጀክቱ ለነዋሪዎች እና ለጎብኚዎች ምቹ የሆኑ የእግር መንገድ፣ የስፖርት እና የመዝናኛ ስፍራዎችን በመፍጠር የከተማዋን የኑሮ ደረጃ ከፍ አድርጎታል።

ከልማቱ ግንባታ ጀምሮ እስከ አሁን ባለው የፓርኮች አስተዳደር እና እንክብካቤ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን በመሳብ ለከተማዋ የቱሪዝም ገቢ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

የወንዝ ዳርቻዎችን ከከተማዋ የትራንስፖርት፣ የኢኮኖሚ እና የመኖሪያ ዞኖች ጋር ማቀናጀት የዘመናዊ ከተማ አስተዳደር ማዕቀፍ ማሳያ ሆኗል።

ኢትዮጵያ የCOP32 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤን ስታስተናግድ አዲስ አበባ የምታቀርበው የታሪክ ሰነድ ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር የተረጋገጠ የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮን ነው።

አዲስ አበባ ለCOP32 የምታደርገው ዝግጅት የዓለም አቀፍ እንግዶችን የማስተናገድ እና የጉባኤ አዳራሾችን የማዘጋጀት ሥራ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የመዲናዋ የወንዝ ዳርቻ ልማት እንደሚያሳየው፣ ከተማዋ የተበላሹ የሥነ ምኅዳር ክፍሎችን በማደስ፣ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ እና የአረንጓዴ ልማት ራእይን በተግባር በመተርጎም ረገድ ያሳየችውን ተጨባጭ ለውጥ ለዓለም የምታበስርበት መድረክ ነው።

ይህ ፕሮጀክት አዲስ አበባ ከአንድ የፖለቲካ ማዕከልነት ባለፈ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተስማምታ የምትኖር፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ዘላቂ የከተማ ዕድገት ተሞክሮን የምታካፍል አረንጓዴ መዲና መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ኩራት ነው።

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: