Search

በመደመር መንግሥት የተጀመረውን የልማት፣ የብልጽግና እና የሰላም እንቅስቃሴ እንደግፋለን፡- ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 75

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሁለተኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ጉባኤውን በይፋ በከፈቱት ወቅት፣ ኢትዮጵያውያን የመደመር መንግሥት የጀመራቸውን ሀገራዊ የልማት፣ የብልጽግና፣ የሰላም እና የአንድነት እንቅስቃሴዎች ከመንግሥት ጎን በመቆም ጫፍ እስኪደርሱ ማስቀጠል እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን አልፋ ዛሬ የተጎናጸፈችውን ነጻነት፣ ዴሞክራሲ፣ ፍቅር እና አንድነት ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሰሃቦች በቸገራቸው ጊዜ “አንድም ሰው የማይበደልበት፣ የእኩልነት፣ የፍቅርና የፍትህ መንግሥት አለና ወደ ኢትዮጵያ (ወደ ሀበሻ) ሂዱ” በማለት ወደ ንጉሠ ነገሥት ነጃሺ መላካቸውን አስታውሰው፣ ከዛሬ 1448 ዓመታት በፊት የጀመረው ይኸው ሰላማዊ ታሪክ የኢትዮጵያን እና የእስልምናን ጥልቅ የሰላም ትሥሥር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን አንድነት ማጠናከር፣ የእስልምና ትምህርት ኢትዮጵያንን በሚመጥን እና ሰላምን በሚያስከብር መልኩ በርትቶ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የመደመር መንግሥት እያከናወናቸው ያሉትን የሪፎርም፣ የልማት እና የብልጽግና ሥራዎች በባለቤትነት ማገዝ እንደሚገባ እና የልማት፣ የሰላምና የአንድነት እንቅስቃሴዎች ተሳክተው ግባቸውን እስኪመቱ ድረስ ከመንግሥት ጎን በመቆም መታገል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አረጋግጠዋል።

ጉባኤው በፍቅር፣ በአንድነትና በመተባበር ተጠናቅቆ ሀገራዊና ሕዝባዊ አጀንዳዎችን እንዲያሳካ ተመኝተዋል።

በላሉ ኢታላ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: