Search

የነዳጅ ጥገኝነትን የሚቀንስ የከተማ ትራንስፖርት ሽግግር

ዓርብ ጥቅምት 27, 2019 74

ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶች በመጠቀም የዜጎቿን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና የኢኮኖሚ ነፃነቷን ለማጠናከር የጀመረችው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያሳየ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተቀየሩ አውቶቡሶች ወደ አገልግሎት መግባታቸው የዚህ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው።

በጥቅምት 22 ቀን 2019 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ 26 ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተቀየሩ አውቶቡሶች ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ ተጨማሪ 400 አዳዲስ የጋዝ አውቶቡሶችም ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ ተገልጿል። ይህ እርምጃ የከተማ ትራንስፖርትን ከማዘመን ባሻገር የሀገራችንን የተፈጥሮ ሀብት ለሕዝብ ተጨባጭ ጥቅም ለማዋል የተጀመረውን ጉዞ የሚያጠናክር ነው።

ኢትዮጵያ በጎዴ የምታመርተውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ መዲናዋ በማምጣት በከተማ ትራንስፖርት ውስጥ መጠቀም መቻሏ የሀገር ውስጥ ሀብትን ወደ ምርታማነት የመቀየር አቅሟን ያሳያል። የተፈጥሮ ሀብትን ለዜጎች ጥቅም በተግባር ማዋል የልማቱ ዋነኛ መሠረት ነው።

የነዳጅ ግዢ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ከሚያስከትሉ ዘርፎች አንዱ ነው። የከተማ አውቶቡሶች በሀገር ውስጥ በሚመረት የተፈጥሮ ጋዝ መንቀሳቀሳቸው ከውጭ የሚገባ ነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለመቆጠብና የሀገራችንን የኢኮኖሚ መቋቋም አቅም ለማጠናከር ያግዛል።

በተጨማሪም የአውቶቡሶች የሥራ ማስኬጃ ወጪ መቀነስ የትራንስፖርት ታሪፍን ለማረጋጋት እና ለተጠቃሚዎች ተመጣጣኝ አገልግሎት ለማቅረብ ዕድል ይፈጥራል። የከተማ ልማት የዜጎችን ዕለታዊ ኑሮ ማሻሻልና በተሻለ የአካባቢ ሁኔታ እንዲኖሩ ማስቻልም ነው።

ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ መሸጋገር የተሽከርካሪዎችን የተወሰኑ የአየር ብክለት አመንጪ ጋዞችና ቅንጣቶች ለመቀነስ ያግዛል። ይህም ለከተማዋ ነዋሪዎች ጤናማ አካባቢ ለመፍጠርና የአረንጓዴ ከተማ ግንባታን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ፕሮጀክቱ የቴክኖሎጂ እና የሀገር ውስጥ አቅም ግንባታንም ያጠናክራል። ጋዙን ከማምረቻ ቦታው ወደ መዲናዋ ማጓጓዝ፣ የጋዝ ማደያዎችን መገንባት እና አውቶቡሶችን ለአዲሱ የኃይል ምንጭ ማስተካከል የቴክኒክ እውቀትን፣ የሰው ኃይል አቅምንና የጥገና ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ዕድል ይፈጥራል።

ይህ እርምጃ የመደመር መንግሥት የልማት ዕይታን በተግባር የሚያሳይ ሲሆን፣ የኢነርጂ፣ የትራንስፖርት እና የቴክኖሎጂ ዘርፎችን አቅም በማቀናጀት የሀገራችንን ሀብት ለጋራ ዓላማ የማዋል ሂደትን ያጠናክራል።

የሀገራችን መዲና እና የአፍሪካ ዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ ማዕከል የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማን ትራንስፖርት ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና አካባቢን የሚጠብቅ ማድረግ የከተማ ልማት ዋነኛ አቅጣጫ ነው።

የተፈጥሮ ጋዝ አውቶቡሶች ከኤሌክትሪክ አውቶቡሶች፣ ከቀላል ባቡርና ከዘመናዊ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ ሲዳብሩ የከተማዋን የኑሮ ሁኔታ የበለጠ ለማሻሻል ያግዛሉ።

በመሆኑም ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተሸጋገሩ አውቶቡሶች ወደ አገልግሎት መግባታቸው የሀገራችንን የተፈጥሮ ሀብት በልማት ለመጠቀም፣ የውጭ ነዳጅ ጥገኝነትን ለመቀነስ እና ዘመናዊ የከተማ ትራንስፖርትን ለማጠናከር የተጀመረው ጉዞ አካል ነው።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: