Search

ከአረንጓዴ ዐሻራ እስከ COP32፡- የኢትዮጵያ የአየር ንብረት አመራር ስኬት

እሑድ ጥቅምት 29, 2019 104

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን፣ የሙቀት መጨመርን እና የምግብ ዋስትና እጥረቶችን ለመታገል አዲስ እና በተግባር የተደገፈ መፍትሔ በሚሻበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የ2027 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ናት።

ሀገራችን ለዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ ከበቃችባቸው ምክንያቶች መካከል በገሃድ ያሳየችው የአካባቢ ጥበቃ ቁርጠኝነት እና ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በስኬት የተገበረችው የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ስኬት ይጠቀሳሉ።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ መተግበር የጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ በኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ ሥራ ከአንድ ቀን መርሐ ግብርነት ወጥቶ ወደ ዘላቂ ሀገራዊ ንቅናቄነት እንዲያድግ አድርጓል፤ ማኅበረሰቡም አካባቢውን መልሶ በማልማት እና በመንከባከብ ረገድ ታሪካዊ አደራውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።

በዚሁ ሀገራዊ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ2011 እስከ 2018 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ይህ አኃዝ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ የምትሰጠውን የላቀ ዋጋ እና የሕዝቦቿን በአንድ ዓላማ የመቆም ተምሳሌትነት በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ይህ ጥረት የሀገራችንን ገጽታ እና ሥነ-ምኅዳር በሰፊው እየቀየረው ይገኛል። ሀገራዊው የደን ሽፋን ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17.2 በመቶ በ2015 ዓ.ም ወደ 23.6 በመቶ አድጓል።

ይህም በአራት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከስድስት በመቶ በላይ ብልጫ ያለው ዕድገት መመዝገቡን የሚያሳይ ሲሆን፣ ሀገራችን እስከ ፈረንጆቹ 2030 የደን ሽፋኗን 30 በመቶ ለማድረስ ለያዘችው ግብ ግዙፍ መሠረት ጥሏል።

ኢትዮጵያ COP32ን እንድታዘጋጅ መመረጧ በድንገት የተሰጠ ዕድል ሳይሆን፣ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ፍትሕ የምታደርገው ቁርጠኛ ጥረት ውጤት ነው።

አዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ዋና ሰለባ በሆኑበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በተግባር ያሳየችው አረንጓዴ ዐሻራ ለሌሎች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ትልቅ ማሳያ ሆኗል።

በዚሁም መሠረት ኢትዮጵያ በCOP32 መድረክ የአካባቢ ጥበቃ እና የምግብ ዋስትና ትሥሥርን ለዓለም ታስተዋውቃለች፣ የታዳሽ ኃይል እና የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ተሞክሮዋን በማካፈል የአዳጊ ሀገራትን ድምፅ ታሰማለች፣ አየር ንብረት ፋይናንስ ለአዳጊ ሀገራት በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ በሚደረገው ድርድር ላይ በዋና አቅራቢነትና መሪነት ትሰልፋለች።

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: