የአዲስ አበባ ወንዞች እና የኮሪደር መስመሮች ሰዎች የሚዝናኑባቸው፣ ህፃናት የሚጫወቱባቸው፣ ጤናቸውን የሚጠብቁባትና ከዕለት ተዕለት የሥራ ድካም እፎይታ የሚያገኙባት ምቹ ስፍራዎች ሆነዋል።
ይህንን የከተማ ኑሮ ውበትና ትርጉም በተግባር እያሳየች ያለችው አዲስ አበባ፣ የወንዞቿ ዳርቻዎችና የኮሪደር መስመሮቿ ከቀድሞው ገጽታቸው ተላቀው ለመዝናኛ፣ ለእረፍት፣ ለእግር ጉዞና ለማህበራዊ ትሥሥር ምቹ ወደሆኑ የሕዝብ መገናኛ ስፍራዎች እየተቀየሩ ይገኛሉ።
በተለይም በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ መስመሮች ላይ የተገነቡት ዘመናዊ የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች ለልጆች ደስታን፣ ለወላጆች እፎይታን፣ ለቤተሰቦች ደግሞ በጋራ የሚያሳልፉትን ውድ ጊዜ እየፈጠሩ ነው።
ይህም ለሕፃናት እድገትና ደስታ ቅድሚያ የምትሰጥ፣ ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ አካባቢ የምትፈጥር ከተማ የመሆን ጉዟችንን ያመላክታል።
በተመሳሳይ የተስፋፉትና የተዘመኑት የስፖርት መሠረተ ልማቶች የከተማችንን የቱሪዝም መስህብነት ከማሳደግ ባለፈ፣ ለአካል ብቃትና ለጤናማ ኑሮ ማዕከላት እየሆኑ ነው።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የውጭ ዲፕሎማቶች እነዚህን ስፍራዎች ለመዝናኛና ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ እየተጠቀሙባቸው መሆናቸውም የከተማችንን ዓለም አቀፍ ተመራጭነት የሚያጎላ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የአካታች መሠረተ ልማት ግንባታ፣ የፓርኮች ውበትና ምቾት እንዲሁም የተሟላ አገልግሎት መስፋፋት ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች በእኩልነት የሚጠቀሙባቸውን የጋራ ሀብቶች እየፈጠረ ነው።
እነዚህ ስፍራዎች የከተማችን ውበት መገለጫዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የማኅበራዊ ትሥሥር፣ የጤናማ አኗኗርና የሰው ልጅ ደስታ መሠረቶችም ናቸው።
የከተማ ልማት ትልቁ ዓላማ መሠረተ ልማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎች በተገነቡት መሠረተ ልማቶች ውስጥ የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ ማስቻል መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
ስለዚህ እነዚህ የመዝናኛና የእረፍት ስፍራዎች በዕለት ተዕለት ሥራ የደከመውን አዕምሮ ለማደስ፣ ከቤተሰብና ከወዳጆች ጋር ውድ ጊዜ ለማሳለፍ፣ ለአካል ብቃትና ለጤናማ ኑሮ እንድንጠቀምባቸው ሁላችሁንም እንጋብዛለን ብሏል ጽሕፈት ቤቱ።
አዲስ አበባ የምንሠራባት፣ የምንኖርባት፣ የምንዝናናባት፣ ጤናችንን የምንጠብቅባት የቱሪዝም ማዕከል እየሆነች መሆኗንም ጠቅሷል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: