ኢትዮጵያ በብዙ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቀለማት የተዋበች ታላቅ ሀገር ናት። የዚህች ውብ ሀገር እውነተኛ ጥንካሬና ልዩ ማራኪነት የሚጎላው ደግሞ የየራሳቸውን ተፈጥሯዊ ፀጋ ይዘው በተሰናሰሉ የብዝኃነት ኅብሮች ውስጥ ነው።
ባለፉት ዘመናት ልዩነቶቻችንን የመራራቅና የክፍፍል መንስኤ ለማድረግ የተሄዱ አጥፊ መንገዶች ቢኖሩም፣ ዛሬ ግን ብዝኃነታችንን የአንድነታችን መሠረት፣ የጥንካሬያችን ምንጭ እና የጋራ ውበታችን የምናደርግበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።
ይህንን ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በጽኑ መሠረት ላይ ማቆም የሁሉም ስኬቶቻችን መነሻና መድረሻ ነው። ሀገራችን በየዘርፉ የጀመረቻቸውም ሆነ ያሳካቻቸው ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች ከግብርና እስከ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ከሜጋ ፕሮጀክቶች እስከ ከተሞች ውበትና ልማት መሠረታቸው ይኸው ጽኑ አንድነታችንና የጋራ ልፋታችን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምስረታ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “እንደ ሀገር የሚጠብቀንን ፈተና መሻገር የምንችለው እንደ ወንድማማች ተያይዘን እኩል መራመድ ስንችል ብቻ ነው” ብለዋል። ይህም አንድነታችን የትኛውንም ሀገራዊ እና አህጉራዊ ፈተና በጋራ የመሻገሪያችን ብቸኛና ዘላቂ መንገድ መሆኑን ያሳያል።
ይህ ተያይዞ የማደግ፣ አብሮ የመራመድ እና የማሸነፍ ራዕይ እውን ሊሆን የሚችለው እያንዳንዳችንን የሚያስተሳስሩ ወርቃማ እሴቶችን አጣጥመን መጓዝ ስንችል ነው።
ብዝኃነትን ከአንድነት፣ የእምነት ልዩነትን ከእሴት ትሥሥር፣ አካባቢያዊነትን ከሀገር አቀፍ ራዕይ፣ የግል ፍላጎትን ከጋራ ጥቅም፣ የትናንት ትምህርትን ከዛሬ ተግባር እንዲሁም ዐቅምን ከጽኑ አቋም ጋር አዋህደን ስንጓዝ የትኛውም ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ መሰናክል ሊያስቆመን አይችልም።
አካባቢያችንን ማልማታችን እና የግል ፍላጎታችንን ማሳካታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ያንን ፍላጎት ከሀገራችን ሕልውናና የጋራ ተጠቃሚነት ጋር አጣጥሞ መራመድ የሁላችንም የዜግነት ኃላፊነት ነው።
ትናንት የገጠሙንን ፈተናዎች እና ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች ለዛሬው ጉዟችን ስንቅ በማድረግ፣ ዐቅምና አቋማችንን አስተባብረን ከተራመድን፣ ኢትዮጵያን የተመኘንላትንና የሚገባታትን የከፍታ ማዕረግ ማልበስ እንችላለን።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: