Search

የመደመር ራዕይ እና የኢትዮጵያ የወል ትርክት ግንባታ፦ ከጽንሰ ሐሳብ ወደ ተጨባጭ ውጤት

እሑድ ጥቅምት 29, 2019 165

በታሪክ አጋጣሚዎች እና በፖለቲካዊ ውቅሮች ምክንያት የራሷ የሆኑ ውስብስብ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎች ያሏት ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ዓመታት የሀገር ግንባታ ሂደቷን አዲስ መልክ ሊሰጥ የሚችል የትርክት እና የፖሊሲ መዋቅር አስተዋውቃለች።

ይህም መደመር በተሰኘው የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ የሀገር ግንባታ ራዕይ ነው። የመደመር ዕይታ ዋና ዓላማ የነበሩትን መልካም እሴቶች ማስቀጠል፣ የተሠሩ ስህተቶችን ማረም እና የነገዋን ሀገር ለሁሉም የሚበጅ አድርጎ በጋራ መገንባት ነው።

የወል ትርክት ግንባታ በተሳሳተ መንገድ ሲተገበር የአንድን ወገን ታሪክ፣ ባህል ወይም ቋንቋ በሌሎች ላይ በመጫን የመገለል ስሜት ሊፈጥር ይችላል። ይሁን እንጂ የመደመር አስተሳሰብ የሚያሰምርበት መሠረታዊ እውነት የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ እና አስተዋፅኦ በእኩልነት የሚታወቅበት እና የሚከበርበት የጋራ መድረክ መፍጠር እንጂ የአንድ ቡድን የበላይነት መጫን አለመሆኑን ነው።

የልዩነት ነጥቦችን ብቻ ከመንቀስ ይልቅ ሕዝቦችን ለዘመናት አስተሳስረው ያቆዩትን እንደ ዕድር፣ ዕቁብ፣ የደቦ እና ሌሎች በጎ አድራጎት ባህሎች የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ማጎልበት ላይ ያተኩራል።

የመደመር መንግሥት የወል ትርክት ግንባታን ከመፈክር ባለፈ ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመቀየር የተለያዩ መዋቅራዊ እና ፕሮጀክት ተኮር ሥራዎችን አከናውኗል።

በዚህም በሕግ አውጪው አካል ገለልተኛ ሆኖ የተዋቀረው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ባልተለመደ መልኩ በዜጎች እና በተለያዩ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ቡድኖች መካከል ባሉ መሠረታዊ ልዩነቶች ላይ ውይይት እንዲደረግ መድረክ ከፍቷል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ በግንባር ቀደምትነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ የነጻነትና የእኩልነት ምልክት ተደርጎ በድምቀት እንዲገነባ መደረጉ፣ የጋራ ኩራትን እና ታሪካዊ ትሥሥርን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

የዜጎችን ቀጥተኛ ተሳትፎ በሚጠይቀው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ሂደቱ ላይ የሁሉም ክልሎች ሕዝቦች በጋራ እንዲሳተፉ መደረጉ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የማኅበራዊ አንድነት እና የትውልድ ትሥሥር ማሳያ አዎንታዊ እንቅስቃሴ ሆኖ አገልግሏል።

የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን የወል ትርክት ለመገንባት የዘረጋው መንገድ ብዝኃነትን ያቀፈ፣ የጋራ ታሪክን የሚያከብር እና የነገን ተስፋ የሚያልም ነው።

እስከ አሁን የተከናወኑ የቅርሶች ልማት፣ የሀገራዊ ምክክር መድረክ እና የጋራ የልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው።

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: