Search

የተፈጥሮ ሀብትን የማልማት እና ለቀጣናዊ ብልጽግና የመጠቀም ሀገራዊ ጉዞ

እሑድ ጥቅምት 29, 2019 95

ኢትዮጵያ የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር ተፈጥሮ ሀብቶቿን ለዜጎቿ ሁለንተናዊ እድገትና ለቀታናዊ የጋራ ብልጽግና የማዋል ሉዓላዊ መብቷን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።

የውሃ፣ የማዕድን፣ የግብርና እና የኃይል ሀብቶቿን ለልማት ለማዋል በፍትሐዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለመጠቀም ያላትን ጽኑ አቋምም በተደጋጋሚ አሳይታለች።

በኢትዮጵያ አውድ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የልማት፣ የሉዓላዊነት እና የብሔራዊ ጥቅም መሠረት ነው። የአጠቃቀሙ መርህም በሁለት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ የተመሠረተ ነው። አንደኛው የሀገራችንን ሕዝብ ከድህነት ማውጣት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቀጣናዊ ትሥሥርና ትብብርን ማጠናከር ነው።

ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትልቁ ማሳያ ነው። ግድቡ የሀገራችንን የኃይል ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር፣ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር እያጠናከረ ይገኛል።

በተመሳሳይ የከርሰ ምድር ሀብቶችን በማልማትና የማዕድን ዘርፍ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት ሀገራዊ ገቢን ከማሳደግ ባለፈ፣ የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ለማፋጠን እየተሠራ ይገኛል።

የሀገራችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም የውስጥ አቅምንና የዜጎችን ቀዳሚ ፍላጎት ማዕከል ያደረገ ነው። በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የውጭ ሀገር ነዋሪ ዜጎችን መብትና ክብር ከማስጠበቅ ባሻገር፣ በሀገር ግንባታ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ናቸው።

በተጨማሪም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በንግድ፣ በጋራ መሠረተ ልማት እና በደኅንነት ጉዳዮች ትብብርን ማስፋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። ይህም በዓለም አቀፍ መድረኮች የሀገራችንን ድምፅና ብሔራዊ ጥቅም በግልጽ ለማስጠበቅ አስችሏል።

በብሪክስ አባልነት የደቡብ-ደቡብ ትብብርን፣ የንግድ ግንኙነትን፣ የፋይናንስ አማራጮችን እና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማስፋት እየተሠራ ነው። በተመሳሳይ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የዓለም አቀፍ ተቋማት የአፍሪካን ነባራዊ ሁኔታና ፍላጎት በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲሻሻሉ የሀገራችን አቋም በተደጋጋሚ ተንጸባርቋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የባሕር በር ጉዳይ ለሀገራችን ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትና የዓለም አቀፍ ንግድ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል። ኢትዮጵያ የባሕር በር እና የወደብ አማራጮችን በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች፣ በጋራ ጥቅምና በቀጣናዊ ትብብር መርህ ለማረጋገጥ እየሠራች ትገኛለች።

በሌላ በኩል የሀገራችንን የልማት ጉዞ ያልተመቻቸው አካላት በተለያዩ መንገዶች እክል ለመፍጠር ቢሞክሩም፣ ኢትዮጵያ ከተደቀኑባት ፈተናዎች ተሻግራ ወደፊት መጓዟን በመቀጠሏ የልማት ጥረትና የሉዓላዊነት አቋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿን በራሷ አቅም እና በሉዓላዊ መብቷ ለማልማት፣ የዜጎቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር የጀመረችውን ጉዞ በጽናት ቀጥላለች።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: