በአሁኑ ወቅት መላው ዓለም በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ለከባድ ሥነ-ምህዳራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተዳርጓል።
በተለይም ለካርቦን ልቀት አነስተኛ አስተዋጽኦ ያደረገችው አፍሪካ፣ የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ በመሆን አውዳሚ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የበርሃማነት መስፋፋት እና የሰደድ እሳት እየተፈራረቁባት በከፍተኛ ፈተና ውስጥ ትገኛለች።
በፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት ወቅት በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት ይህንን አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግር ለመቋቋም የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ቢገቡም፣ ቃላቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል።
በዚህም ምክንያት በርካታ ሀገራት እጃቸውን አጣጥፈው የበለፀጉትን ሀገራት የተስፋ ቃል በመጠበቅ ተጨማሪ ጊዜያቸውን እያባከኑ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ግን ይህንን የተጎጂነት እና የጠባቂነት ትርክት በመስበር የተለየ መንገድ መርጣለች። የችግሩን መፍትሔ ለማምጣት ቃል የገቡ የበለፀጉ ሀገራትን ቁጭ ብሎ ከመወትወት እና የውጭ ድጋፍ ከመጠበቅ ይልቅ፣ የመደመርን ፍልስፍና እንደ አየር ንብረት ተነሣሽነት መርሕ አድርጋ በመጠቀም በራሷ አቅም ወደ ዐበይት ተግባራት ገብታለች።
ከመደመር መሠረታውያን አንዱ የሆነው "ተነሣሽነት" ሌሎችን ከመጠበቅ እና ከማማረር ወጥቶ ውስጣዊ ጸጋዎችን አስተባብሮ ለመፍትሔ መሥራት እና ለሌሎችም መንገድ ጠራጊ መሆንን የሚያመለክት ነው።
ኢትዮጵያ ይህንን መርሕ መሬት ላይ በማውረድ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሆን ተግባራዊ እና ዘላቂ የመፍትሔ አርዓያ መሆን ችላለች።
በዚሁ የመደመር ተነሣሽነት መሪነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ በተካሄዱ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች በ8 ዓመታት ውስጥ 56 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል።
ይህ ታሪካዊ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከሀገር ውስጥ ፍላጎት ባለፈ ከአፍሪካ ኅብረት የ2063 አጀንዳ፣ ከታላቁ አረንጓዴ ግንብ እና ከተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር ሙሉ በሙሉ የተስማማ እና የተጣጣመ ነው።
በዚሁ ጥረት የብሔራዊ ደን ሽፋኗን ከ17.2 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ማሳደግ ችላለች። ይኸው አረንጓዴ በረከት ከራሷ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት የችግኝ እና የልምድ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች።
ይህ በተግባር እና መሬት ላይ በሚታይ ውጤት የተደገፈ ጥረት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አደራዳሪ እና የታማኝ አፍሪካ ድምፅ እንድትሆን አስችሏታል።
የበለፀጉ ሀገራት የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ በሞራላዊ የበላይነት ለመጠየቅ የሚያስችላትን አቅም የፈጠረላትም ይኸው መሬት ላይ ያለው እውነተኛ ሥራዋ ነው።
ይህ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አርዓያነቷ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) እንድታዘጋጅ ታሪካዊ ኃላፊነት ሰጥቷታል።
የመደመር ተነሣሽነት እሳቤ በአየር ንብረት ምላሽ ዙሪያ ሀገራዊ ክብርን ያስጠበቀ፣ አህጉራዊ አንድነትን ያጠናከረ እና የዓለም አቀፍ መሪነትን ያረጋገጠ ሕያው ምስክር ሆኗል።
ሙሉ እና ትክክለኛ የጉባኤውን መረጃዎች ከምንጩ ለማግኘት ሁልጊዜም ትክክለኛውን የኮፕ-32 ይፋዊ ድረ-ገጽ https://cop32ethiopia.et/ ይጠቀሙ።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: