Search

የኮፕ 32 ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እና የአፍሪካ አየር ንብረት ድምፅ

ረቡዕ ኅዳር 02, 2019 79

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተባባሰ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ለመመከት የሚደረገው የጋራ ምላሽ የጀመረው በ1980ዎቹ አጋማሽ ነበር።

ይህ ጥረት እ.አ.አ በ1992 በሪዮ ጉባኤ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት (UNFCCC) እንዲጸድቅ መንገድ የከፈተ ሲሆን፣ ስምምነቱ በ1994 በይፋ ሥራ ላይ ውሏል።

ዋና ዓላማውም የከባቢ አየር ሙቀት መጠንን እና የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን በማረጋጋት ሥነ-ምህዳሩ እንዲጠበቅ፣ የምግብ ዋስትና እንዳይናጋ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት እንዲረጋገጥ ማድረግ ነው።

የስምምነቱ የበላይ አካል የሆነው የመጀመሪያው የፓርቲዎች ጉባኤ (COP1) በ1995 በበርሊን ከተካሄደበት ጊዜ ጀምሮ፣ በየዓመቱ እስከ 80 ሺህ የሚደርሱ ተሳታፊዎችን የሚያስተናገድ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የውሳኔ መድረክ በመሆን አድጓል።

በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የኮፕ ጉባኤዎች ትኩረት ያደረጉት የልቀት መጠንን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተቋማዊ ማዕቀፎችን በመዘርጋት እና ታሪካዊ ኃላፊነትን መሠረት በማድረግ የበለጸጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የዕውቀት ሽግግር ድጋፍ እንዲያደርጉ ግዴታ በመጣል ላይ ነበር።

ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ ድጋፎች፣ ቴክኖሎጂዎች እና የንግድ ስትራቴጂዎች በዋናነት የልቀት ቅነሳ ሥራዎችን ብቻ የደገፉ ሲሆን፣ እንደ ጎርፍ መከላከያ፣ የአየር ንብረት-ስማርት ግብርና እና ማኅበራዊ ጽናትን የመገንባት የኮፕ መላመድ አቅጣጫዎች አነስተኛ ትኩረት እና የፋይናንስ ክፍተት ነበረባቸው።

የአፍሪካ አህጉር እና በታዳጊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሀገራት ለዓለም አቀፍ የልቀት መጠን የሚያበረክቱት ድርሻ ከአራት በመቶ በታች ቢሆንም፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ከባድ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ግን በግንባር ቀደምትነት እየተጋፈጡ ይገኛሉ።

ባለፉት ዓመታት በሞሮኮ፣ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በግብፅ በተካሄዱት ጉባኤዎች የአፍሪካን ድምፅ ለማሰማት ጥረቶች ቢደረጉም፣ የፋይናንስ እና የፖሊሲ እኩልነት አለማግኘት ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ግን የአየር ንብረት መላመድ ጉዳይ እንደ ሕልውና እና ልማት ጉዳይ መታየት እንዳለበት አጽንኦት ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሠረት የዓለም አቀፍ የመላመድ ፋይናንስን እስከ 2035 በሦስት እጥፍ ለማሳደግ ግቦች ተቀምጠዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2027 የCOP32 ጉባኤን ለማስተናገድ መመረጧ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለዘላቂ ልማት ያላትን ጽኑ ቆራጥነት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የሚያሳይ ታሪካዊ እርምጃ ነው።

ዝግጅቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አነስተኛ የልማት ደረጃ ባላቸው እና የባህር በር የሌላቸው አፍሪካዊ ሀገራት ስም የተመዘገበ በመሆኑ ልዩ ትርጉም አለው።

ኢትዮጵያ ያከናወነቻቸው እንደ «አረንጓዴ አሻራ» የመሳሰሉ ግዙፍ የደን ልማት መርሃ-ግብሮች፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ የስንዴ ልማት ጥረቶች፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና የታዳሽ ኃይል አጠቃቀም መስፋፋት የልቀት ቅነሳን እና የአየር ንብረት መላመድን በአንድ ላይ ማቀናጀት እንደሚቻል ለዓለም ያሳየችባቸው ሕያው ማረጋገጫዎች ናቸው።

ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ አህጉር COP32ን ማስተናገድ የሚያስገኘው ትልቁ ስትራቴጂካዊ ትርፍ፣ አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንድታሰማ እና ተጋላጭነቷን ወደ ኢኮኖሚያዊ እድል እንድትቀይረው ማስቻሉ ነው።

በተለይም አፍሪካ ያላትን ውድ አረንጓዴ ማዕድናት እና የኢነርጂ አቅም በመጠቀም ከጥሬ ዕቃ ላኪነት ወደ ሀገር ውስጥ ማቀነባበር እና የኢንዱስትሪ ሽግግር የመሸጋገር አቅጣጫ ለመንደፍ ወሳኝ እድል ይፈጥራል።

በውጤቱም፣ ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ስትመራ የራሷን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት፣ የውስጥ ጽናት እና የረጅም ጊዜ የልማት ራዕይ ከፍ አድርጋ የምታስቀጥልበት ታሪካዊ አርአያነት ይኖራታል።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: