Search

ገጠርን ከከተማ ያስተሳሰረው የልማት እመርታ እና ሀገራዊ ትሩፋቶቹ

ረቡዕ ኅዳር 02, 2019 42

ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን እና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጉዞ የሀገራችን የኢኮኖሚ ጀርባ አጥንት የሆነው የገጠር ማኅበረሰብ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

ለዘመናት የገጠሩ አምራች ኃይል ከተማን የመመገብ እና ሀገራዊ ኢኮኖሚውን የመሸከም ታላቅ ኃላፊነት ቢወጣም በቂ መዋቅራዊ ድጋፍ እና ዘመናዊ መሠረተ ልማት ሳያገኝ መቆየቱ ብዙዎች የሚስማሙበት ሀቅ ነው።

የመደመር መንግሥት ግን ይህንን አስተሳሰብ በመቀየር ገጠርን ከከተማ ጋር በተሳለጠ መልኩ የልማት፣ የሥልጣኔ እና የብልፅግና ማዕከል ያደረገ አዲስ የፖሊሲ አቅጣጫ እየተከተለ ነው።

ይህ እሳቤ ገጠር እና ከተማን በጥብቅ በማስተሳሰር ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር እና አርሶ አደሩ ባለበት ሆኖ የሥልጣኔ እና ዘመናዊ ሕይወት ተጠቃሚ እንዲሆን እያስቻለ የሚገኝ መሠረታዊ ሽግግር ነው።

በከተሞች ተጀምሮ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበው የኮሪደር ልማት አሁን ወደ ገጠር ቀበሌዎች እና ሞዴል መንደሮች መስፋፋቱ የገጠሩን ሕይወት ገጽታ ሙሉ በሙሉ እየቀየረው ይገኛል።

በሞዴል መንደሮች የተዘረጉት የጽዱ መኖሪያ ቤቶች ዲዛይን፣ ንጽህናቸውን የጠበቁ የተለዩ የእንስሳት በረቶች፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የመንገድ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነት አርሶ አደሩ ከተሜነትን ሳይመኝ በገዛ ቀዬው ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኝ አድርገዋል።

ይህ የገጠር ኮሪደር ልማት ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት በመግታት፣ አምራቹ ኃይል በገዛ ቀዬው በሰላም እና በደስታ እየኖረ አምራችነቱን እንዲያጎለብት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

የገጠሩ አኗኗር ከማዘመኑ ጎን ለጎን የግብርናው ዘርፍ የምርታማነት እመርታ አሳይቷል። ቀደም ሲል ተበጣጥሰው እና ባህላዊ አሠራርን ተከትለው አነስተኛ ምርት ይሰጡ የነበሩ ማሳዎች በኩታ ገጠም እርሻ ተደራጅተው በሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ታግዘዋል።

የግብርና ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር እንዲገቡ መደረጉ አርሶ አደሩ ትራክተሮችን እና ኮምባይነሮችን በስፋት በመጠቀም የድካም እና የምርት ብክነትን እንዲቀንስ አድርጎታል።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አርሶ አደሩ በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ እንዲያመርት በማድረግ ኢትዮጵያን ለዘመናት የኖረችበትን የስንዴ ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ በማላቀቅ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንድትችል አድርጓታል።

በሌላ በኩል በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አማካኝነት በወተት፣ በእንቁላል፣ በዶሮ ሥጋ፣ በማር እና በዓሣ እርባታ ዘርፎች የተመዘገበው አስደናቂ የምርት ዕድገት የገጠሩን ማኅበረሰብ የሥነ-ምግብ እና የምግብ ዋስትና በዘላቂነት እያረጋገጠ ነው።

አርሶ አደሩ ከጓሮው የሚያመርታቸው እነዚህ ምርቶች ለራሱ ቤተሰብ የጤናማ አመጋገብ ምንጭ ከመሆናቸው ባለፈ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙለት የብልፅግናው ምንጭ ሆነውታል።

ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር ደግሞ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በተከናወኑ የተቀናጁ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሄክታር መሬት አገግሞ ወደ ምርታማነት እንዲመለስ ተደርጓል። 

በገጠር እና በከተማ መካከል የተፈጠረው ቀጥተኛ የገበያ ትስስር እና የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች መስፋፋት የደላሎችን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ያስቀረ ነው።

አርሶ አደሩ ያመረተውን ትርፍ ምርት በቀጥታ ለከተማው ሸማች ማቅረብ መቻሉ ከአምራችነቱ ተገቢውን የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲያገኝ ሲያስችለው፣ በከተሞች በኩል ደግሞ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትልቅ እፎይታ ሰጥቷል።

የገጠሩ ሕይወት መሻሻል እና የአምራችነቱ ማደግ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገታችን የሚሰጠው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው።

ለስንዴ እና ለሌሎች የምግብ ዕቃዎች ይወጣ የነበረውን በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት የማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋትን ፈጥሯል።

በተጨማሪም በገጠር የተመረተው ትርፍ የምግብ እና የእንስሳት ተዋጽኦ ለሀገራችን የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች በቂ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት በመሆን የኢንዱስትሪውን ዘርፍ እየደገፈ ይገኛል።

ከሁሉም በላይ በአካል እና በአእምሮ የበለጸገ ጤናማ ትውልድ በመገንባት፣ ኢትዮጵያ በምግብ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠላትና በራሷ አቅም የምትቆም ታላቅ ሀገር እንድትሆን አስተማማኝ መሰረት ጥሏል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: