Search

ከበርሊን እስከ አዲስ አበባ የዘለቀው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የሦስት አሥርተ ዓመታት ታሪካዊ ጉዞ

ረቡዕ ኅዳር 02, 2019 114

 ዓለማችን እየበረታባት በመጣው የአየር ንብረት ቀውስ ምክንያት ለከፋ ድርቅ፣ ለተደጋጋሚ ጎርፍ፣ ለከባድ አውሎ ነፋስ፣ ለሰደድ እሳት እንዲሁም ለመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተጋልጣለች።

የሙቀት መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በርካታ ሀገራት በከፍተኛ የሙቀት ማዕበል እየተመቱ የሰው ልጆች ህይወት አልፏል፤ በሰሜን እና ደቡብ ዋልታዎች የሚገኘው የበረዶ ግግር መቅለጥ ደግሞ የባሕር ወለል መጠን እንዲጨምር በማድረግ የባሕር ዳርቻ ከተሞችን የመስመጥ አደጋ እንዲጋረጥባቸው ዳርጓቸዋል፤ ሌሎቹም በስጋት እንዲኖሩ ፈርዶባቸዋል።

ይህንን የበረታ የዓለማችንን ስጋት ለመግታት እና ምድራችን ከተጋረጠባት የህልውና አደጋ ለመታደግ እ.አ.አ በ1992 የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት (UNFCCC) ተመሰረተ።

ይህ ስምምነት ሀገራት የዓለም አቀፍ አማካይ የሙቀት መጠን መጨመርን እና የከፋ ጉዳቱን ለመግታት በጋራ የሚቆሙበትን መድረክ የፈጠረ ሲሆን፣ ስምምነቱን የፈረሙ ሀገራት በየዓመቱ የሚያደርጉት ስብሰባም የዓለም አቀፉ አየር ንብረት ጉባኤ (COP) በመባል ታወቀ።

ከ33 ዓመታት በዘለለው የኮፕ ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ ኢትዮጵያ ጉባኤው ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ የአየር ንብረት ፍትህ እንዲረጋገጥ እና የታዳጊ ሀገራት ድምፅ እንዲሰማ ንቁ ተሳትፎ ስታደርግ ቆይታለች።

ከጥያቄም አልፋ የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም አረንጓዴ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀርጻ በመተግበር የጠባቂነት ትርክትን በመስበር ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም አርዓያ ሆናለች። ዛሬ ደግሞ ከተሳታፊነት አልፋ 32ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማዘጋጀት በባለቤትነት የተመረጠችበት ደረጃ ላይ ደርሳለች።

 ኢትዮጵያ ይህንን ከ80 ሺህ በላይ ዓለም አቀፍ እንግዶች እንዲሁም ከ4 ሺህ በላይ ጋዜጠኞች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቅበትን ታላቅ ጉባኤ ለማስተናገድ መመረጧ በራሱ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው።

ይህ ድል የተገኘው ደግሞ ሀገራችን ከአረንጓዴ ዐሻራ እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በሠራችው አስደማሚ ሥራ ነው።

ጉባኤው ይህን ጥረቷን በተጨባጭ ለዓለም የምታሳይበት፣ በርካታ የውጭ ልዑካንን በማስተናገድ የሆቴል እና ቱሪዝም ኢንዱስትሪዋን የምታነቃቃበት እንዲሁም የአየር ንብረት ፋይናንስ ተጠቃሚነቷን የምታጎለብትበት ታሪካዊ አጋጣሚ ይሆንላታል።

የጉባኤው የመጀመሪያው ታሪካዊ ስብሰባ እ.አ.አ በ1995 በጀርመን በርሊን ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ እስካሁን 4 የአፍሪካ ሀገራት ለ5 ጊዜያት ያክል ጉባኤውን የማስተናገድ እድል አግኝተዋል።

ሞሮኮ 7ኛውን እና 22ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ያስተናገደች ሲሆን፣ ኬንያ 12ኛውን፣ ደቡብ አፍሪካ 17ኛውን እንዲሁም ግብጽ ደግሞ 27ኛውን ጉባኤዎች ለማስተናገድ ችለዋል።

ከዛሬ 31 ዓመታት በፊት በጀርመን በርሊን በተካሄደው የመጀመሪያው ጉባኤ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የሚሰጡትን ምላሽ ለማጠናከር ድርድር ማድረግ የጀመሩበት ነው።

ከሁለት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ. በ1997 የበለጸጉ ሀገራት ካርቦን ልቀታቸውን እንዲቀንሱ በሕግ የሚያስገድደው ታዋቂው "የኪዮቶ ፕሮቶኮል" ጸደቀ።

ይሁን እንጂ ስምምነቱ ጸድቆ ሕጋዊ አስገዳጅነት አግኝቶ ሥራ ላይ ለመዋል እ.አ.አ እስከ 2005 ድረስ መጠበቅ ነበረበት። የመጀመሪያው የኪዮቶ ፕሮቶኮል የትግበራ ወቅት ከ2008 እስከ 2012፣ ሁለተኛው ደግሞ ከ2013 እስከ 2020 ዘልቋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ እ.አ.አ. በ2011 ካናዳ "ስምምነቱ ሁለቱን ትላልቅ የካርቦን ጋዝ አመንጪ ሀገራት ማለትም አሜሪካን እና ቻይናን አያካትትም" በማለት የመጀመሪያዋ ከኪዮቶ ፕሮቶኮል እራሷን ያገለለች ሀገር ሆናለች። ይህም ዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ ጉዞ ሁልጊዜ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ያሳየ ክስተት ነበር።

እ.አ.አ በ2009 በዴንማርክ ኮፐንሃገን የተካሄደው 15ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP15) ሕጋዊ አስገዳጅነት ያለው ስምምነት ላይ ሳይደርስ በውዝግብ ተጠናቀቀ፡፡

ሆኖም በኢንዱስትሪ በበለጸጉ ሀገራት በኩል ለታዳጊ ሀገራት በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የተገባበት እና የለውጥ ጭላንጭል የታየበት ነበር።

 የዓለም አቀፉ አየር ንብረት ዲፕሎማሲ ትልቁን የማዕዘን ድንጋይ ያስቀመጠው እ.አ.አ በ2015 በፈረንሳይ በጸደቀው "የፓሪስ ስምምነት" ነው።196 አገራት የፈረሙት እና እ.አ.አ በ2016 ሥራ ላይ የዋለው ይህ ስምምነት የዓለምን የሙቀት መጠን ጭማሪ ከቅድመ-ኢንዱስትሪ ዘመን አንጻር ሲነጻጸር ከ2 ዲግሪ ሴልሺየስ በታች ለማድረግ እና ወደ 1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ ለመገደብ ግብ አስቀመጠ።

 የፓሪስ ስምምነት አዳጊ እና ተጋላጭ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያደርጉትን ጥረት በፋይናንስ እና በአቅም ግንባታ ለመደገፍ አዲስ ምዕራፍ ከፈተ። ይህንን ተከትሎ እ.አ.አ በ2021 በተካሄደው የግላስጎው ጉባኤ ሀገራት የልቀት መቀነሻ ዕቅዶቻቸውን እንዲገመግሙ እና ለመጀመሪያ ጊዜ የድንጋይ ከሰል አጠቃቀምን ለመገደብ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።

ከኮፕ 22 (COP22) እስከ ኮፕ 28 (COP28) በተካሄዱት የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤዎች፣ የፓሪስ ስምምነትን ወደ ሙሉ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ የሕግ እና የአሰራር ደንቦች በመውጣታቸው የዓለም አቀፍ የካርቦን ገበያ ህጎች መፅደቅ ችለዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ሀገራት የድንጋይ ከሰል አጠቃቀምን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስ፣ እስከ 2030 ድረስ የታደሰ ኃይል አቅምን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ እና ለመጀመሪያ ጊዜ ከቅሪተ አካል ነዳጅ ወደ ንፁህ ኃይል ለመሸጋገር ታሪካዊ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በተጨማሪም የአየር ንብረት አደጋ ለሚደርስባቸው ታዳጊ ሀገራት የቴክኒክ ድጋፍና የፋይናንስ ማገገሚያ የሚሆን የጉዳትና ማገገሚያ ፈንድ (Loss and Damage Fund) መቋቋሙ ለታዳጊ ሀገራት ትልቅ እፎይታን ሰጥቷል።

ኮፕ 29 (COP29) ጀምሮ እስከ ኮፕ 32 (COP32) ባሉት ጉባኤዎች ደግሞ ትኩረቱ ታዳጊ ሀገራትን ለመደገፍ የሚውል አዲስ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፋይናንስ ግብ በማስቀመጥ፣ የደኖች መቆረጥን ማስቆም እና የብዝሃ-ሕይወት ጥበቃን በስፋት ማሳደግ ላይ አተኩሯል።

እንዲሁም የዓለምን የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም ወደ ንጹህ አየር ንብረት ተስማሚ አማራጮች የማሳደግ ውሳኔዎች ያስተላፉ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2027 በአዲስ አበባ የሚካሄደው ኮፕ 32 (COP32) የአፍሪካን ቅድመ-አንደኝነት ነጥቦች፣ ለአየር ንብረት ፍትህ የሚደረጉ ጥረቶችን እና የአረንጓዴ ልማት ኢንቨስትመንቶችን የበለጠ የሚያጎለብቱ ዓለም አቀፍ ውሳኔዎች የሚያስተላፍበት ታሪካዊ መድረክ ይሆናል።

 

በዛሬው እለትጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የበርካ ሀገራት መሪዎች እየተሳተፉበት 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ31) “ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” በሚል መሪ ቃል በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።

 

ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ኮፕ 32ትን አስተናጋጅነት ከቱርኪዬ ስትረከብ በእንግዳ ተቀባይነቱ ወደር የማይገኝለት ሕዝባችን፤ በዓለም የምንታወቅበትን ቡና በተወዳጅ አቀራረቡ አሰናድቶ ከ80 ሺህ የሚልቁ እንግዶቹን ለማስተናገድ ከወዲሁ በርካታ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል።

 በናትናኤል ጸጋዬ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: