Search

ሉዓላዊነትንና ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የሚችል ዘመኑን የዋጀ ሠራዊት ተገንብቷል፦ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ቅዳሜ ኅዳር 05, 2019 134

ታሪካዊ የውጫዊ ጫና ፈተናዎችን ያለፈችው ኢትዮጵያ ዛሬም ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ በቂ ዝግጁነት ያለው ጠንካራ ሠራዊት እየገነባች መሆኗን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገልጸዋል።

የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ በፒ.ኤስ.ሲ እና በማስተርስ መርሐ ግብር ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የሠራዊቱ ግንባታ በሰው ኃይል ጥራት፣ በሙያዊ ክህሎት፣ በአመራር ብቃትና በቴክኖሎጂ አቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል።

የሠራዊቱ ግንባታ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በጥራት፣ በብቃት እና በዘመናዊ የውጊያ አቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አንስተዋል።

የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ጥቅም እና ሕዝብን ደህንነት ለማስጠበቅም በዘመናዊ አመራርና በቴክኖሎጂ የዳበረ ሠራዊት እየተገነባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአሁኑና የወደፊቱ የጦርነት አካሄድ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እውቀትና የመረጃ አጠቃቀም ብቃት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የሠራዊቱ አመራሮች ዲጂታል ቴክኖሎጂን፣ የጂፒኤስ (GPS) ሥርዓትን፣ የኮምፒውተር አጠቃቀምንና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) በብቃት መጠቀም እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በተለይም የአመራር ኃላፊነት የሚሸከሙ መኮንኖች መረጃን በትክክል በመተንተን፣ ቴክኖሎጂን በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ማዋልና ከዘመኑ ወታደራዊ አሠራር ለውጦች ጋር መራመድ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የአዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ የሥልጠና ካሪኩለሙን በማዘመን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማጠናከር እና አቅሙን በማሳደግ ለቀጣዩ የወታደራዊ አሠራር ለውጥ ብቁ የሆኑ አመራሮችን ማፍራት እንዳለበት ያሳሰቡት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ኮሌጁ ከኢትዮጵያ ባሻገር ከተለያዩ የአፍሪካና ዓለም ሀገራት የሚመጡ መኮንኖችን የሚያሰለጥን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ማዕከል እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመራቂ መኮንኖችም በኮሌጁ ያገኙትን እውቀትና ልምድ በተግባር በማዋል፣ ራሳቸውን በቀጣይነት በማብቃት እና ከዘመኑ የቴክኖሎጂ እድገት ጋር በመራመድ ለሠራዊቱ ዝግጁነትና ለሀገር ደኅንነት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: