Search

የኢትዮጵያ የፕሮጀክት አፈጻጸም አዲስ ምዕራፍ

ቅዳሜ ኅዳር 05, 2019 113

የኢትዮጵያ የልማት እና የፕሮጀክት አፈጻጸም ጉዞ ከቀደምት ጥልቅ መዋቅራዊ ችግሮች ተላቅቆ ወደ አዲስ እና አስተማማኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

በቀድሞ ጊዜ በልማት ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ቢደረግም፣ በቂ የአዋጭነት ጥናት እና የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ዋስትና ሳይኖር በመጀመራቸው ከፍተኛ የሀብት ብክነት እና የጊዜ መጓተት ያጋጥም ነበር። በርካታ ፕሮጀክቶች ተጀምረው በሂደት መቆማቸው ለኢኮኖሚው ከባድ ጫና ፈጥሮ ቆይቷል።

ከዚህ የፕሮጀክት አፈጻጸም ድክመት ማሳያዎች መካከል አንዱ የስኳር ዘርፍ ኢንዱስትሪ ነው። ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት ተይዞላቸው የተጀመሩት አሥሩ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ በከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ እና በአሥር ቢሊዮኖች የሚቆጠር የዕዳ ሸክም እንዲቆሙ ተደርገዋል።

የስኳር ፕሮጀክቶቹ አለመሳካት በወጣባቸው ወጪ ብቻ የተወሰነ ውድቀት አልነበረም። የውስጥ ፍላጎትን ማሟላት ባለመቻሉ ከውጭ ለማስመጣት ግዙፍ የውጭ ምንዛሬ እንዲባክን አድርጓል። ዘርፉ የውጭ ዕዳን ወርሶ በመቀጠሉ ማኅበራዊ እና ፊስካል ጫናዎችን ፈጥሯል።

ይህ የዘገየ እና የተበላሸ የፕሮጀክት አፈጻጸም ባሕል በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ስብራት አስከትሏል። ፕሮጀክቶች ላይ የተሟላ የጥናት እና የበጀት ዲሲፕሊን ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ጥሪቷን ያለአግባብ አባክናለች።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የብዙ ዓመት ካፒታል በጀት አወጣጥ፣ የግዥ መረጃ ግልጽነት እና የንብረት መዝገብ አያያዝ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መቆየቱ፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የዋጋ ግሽበት ማክሮ ኢኮኖሚውን ፈትነዉታል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት ግን ይህንን የተዛባ አካሄድ ለመቀልበስ ሰፊ የሕግ፣ የፋይናንስ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

በ2012 ዓ.ም የወጣው የሕዝብ ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር አዋጅ እና የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፕሮጀክት አመራሩን በሕግ እና በፖሊሲ ማዕቀፍ ለመምራት ጠንካራ መሠረት ጥለዋል።

ይህ አዲስ የፕሮጀክት አፈጻጸም ባሕል የከፍተኛ አመራር ቀጥተኛ ክትትልን፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን፣ ጥራትን እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ቅድሚያ በመስጠት የልማት እንቅስቃሴውን አቅጣጫ ቀይሮታል።

በዚህ የተለወጠ የፕሮጀክት አፈጻጸም ባሕል ትንሣኤ ያገኙ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ለኢኮኖሚው ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረግ ጀምረዋል።

በአፈጻጸም ችግር ፈተና ውስጥ ገብቶ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከጥፋት የታደገው ይኸው አዲስ የፕሮጀክት አስተዳደር አካሄድ ነው።

በተመሳሳይ ለ18 ዓመታት ተጓትቶ የነበረው የመገጭ መስኖ ግድብ በይፋ ተመርቆ 17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት አቅም የፈጠረ ሲሆን፣ ኮይሻ እና አርጆ-ደዴሳ ፕሮጀክቶችም አዲስ ሕይወት ዘርተው ወደ ማጠናቀቂያው ምዕራፍ እየተሸጋገሩ ይገኛሉ።

የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በየጊዜው መገምገም እና ሀብትን በትክክለኛው አቅጣጫ ማሰማራት መቻሉ ለቀጣይ ዘላቂ ዕድገት ዋስትና እየሆነ ነው።

ተጀምረው የቆሙትን ከማንሳት ባሻገር እንደ አዲስ ተጀምረው በጥራት እና በፍጥነት እየተጠናቀቁ ያሉ እና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች የተቋማት፣ የከተሞችን እና የቱሪዝምን ገጽታ ቀይረዋል።  

በገበታ ለሀገር ማዕቀፍ የተገነቡት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እና ጥራት ተጠናቅቀው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው የቱሪዝም መዳረሻዎች ሆነዋል።

በውስጥ በጀት እና በቁርጠኛ አመራር በአጭር ጊዜ የተሠራው የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት የከተማውን ገጽታ፣ የንግድ ከባቢ እና የኢኮኖሚ አቅም በእጅጉ ማሻሻል ችሏል።

እንደ የአብርሆት ሕዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ ሳይንስ ሙዚየም እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ያሉ ፕሮጀክቶች ደግሞ ለአፈጻጸም ፍጥነት እና ጥራት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ብሔራዊ ከፍታዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ በ30 ቢሊዮን ብር ወጪ የምትገነባቸው የጉባ ብሥራት ፕሮጀክቶችም በዚህ ውጤታማ የፕሮጀክት አስተዳደር ማዕቀፍ 24 ሰዓት እየተፋጠኑ ይገኛሉ።

ይህ አጠቃላይ የመሠረተ ልማት አስተዳደር ለውጥ ኢትዮጵያ በራስ አቅም እና በዘላቂ ዕቅድ ማደግ እንደሚቻል ያረጋገጠችበት የሀብት ባለቤትነቷንም ወደ ውጤታማ አጠቃቀም የለወጠበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: