ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትመሰል ሀገር መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተጀመሩ ሥራዎች የአካባቢ ጥበቃ፣ የዘላቂ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ የደኅንነት እና የብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያ ቁልፍ ስልቶች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማፋጠን ለትውልድ ተሻጋሪ ብልጽግናን የማረጋገጥ ብሔራዊ ንቅናቄ መሆኑን አቶ ተመስገን ጠቁመዋል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን የተከለችው ኢትዮጵያ፤ በታዳሽ ኃይል፣ በኮሪደር ልማት፣ በበጋ መስኖ እና በወንዝ ዳርቻ ልማት የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት እየገነባች እንደምትገኝም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ይህንኑ ተግባራዊ ተሞክሮ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ በማስፋት በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ያላትን ተፅዕኖ እያጠናከረች መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቱርክዬ አንታሊያ እየተካሄደ ባለው የCOP31 ጉባኤ ላይ እያደረገች ባለው ንቁ ተሳትፎ እና በከፈተችው መካነ ርዕይ የአረንጓዴ ልማት ስኬቶቿንና ሀገራዊ ትዕምርቶቿን ለዓለም እያስተዋወቀች ነው ብለዋል።
ከአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መሪ ሚናን ከመወጣት ባለፈ የCOP32 ጉባኤ አስተናጋጅ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በአንታሊያው መድረክ ልምዷን እያጋራች እና ከዝግጅቱ ልምድ እየቀሰመች እንግዶቿን በክብር መጥራቷንም ገልጸዋል።
ከአንድ ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሀገራችን የልማት ተሞክሮዋን መሬት ላይ የምታሳይበት፣ ለአየር ንብረት ፍትሕና የልማት ፋይናንስ ገቢራዊነት የምትተጋበት፣ እንዲሁም በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንትና በዓለም አቀፍ አጋርነት ያሉ ዕድሎችን የምታሰፋበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑን አንስተዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: