በመቐለ ከተማ ከተማዋ የተጀመረውን የንግድ እንቅስቃሴ በዘላቂነት ለማስቀጠል፣ ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል እና የንግዱ ማኅበረሰብ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከሰባቱ ክፍለ ከተሞች የንግድ እና የመንግሥት አገልግሎት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የመቐለ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረሕይወት ገብረሥላሴ ናቸው።
አቶ ገብረሕይወት ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሷን ተከትሎ የተጀመረውን ግብይት ማጠናከር፣ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ማስፈን እና ለነጋዴዎች ምቹ የሥራ ሁኔታ መፍጠር የአስተዳደሩ ዋነኛ ትኩረት መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይም ሕገወጥ የንግድ አሠራሮችን በመከላከል የንግዱ ማኅበረሰብ ያለ አንዳች መስተጓጎል ሥራውን እንዲያከናውን በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመድረኩ የሰባቱ ክፍለ ከተሞች የንግድ እና የመንግሥት አገልግሎት ኃላፊዎች በየአካባቢያቸው የሚስተዋሉ የንግድ እንቅስቃሴ ተግዳሮቶችን እና ለዘላቂነቱ መፍትሔ ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ሐሳብ ተለዋውጠዋል።
የንግድ እንቅስቃሴውን በዘላቂነት ማስቀጠል ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊ መልሶ ማገገም፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለነዋሪዎች የሸቀጦች እና አገልግሎቶች ተደራሽነት ወሳኝ ሚና እንዳለውም በውይይቱ ላይ ተመልክቷል።
በአስማረ ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: