Search

በመቐለ ከተማ ባለፉት 30 ቀናት ሰላምን በማስፈን እና ተቋማትን ወደ መደበኛ ሥራ በመመለስ ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ሺሻይ አማረ (ዶ/ር)

ዓርብ ኅዳር 11, 2019 97

በመቐለ ከተማ ባለፉት 30 ቀናት ሰላምን በማስፈን፣ መንግሥታዊ ተቋማትን እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ወደ መደበኛ ሥራ በመመለስ ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የከተማዋ ከንቲባ ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ ያለፉት 30 ቀናት የሥራ አፈጻጸምን ከተለያዩ ቢሮዎች ጋር በገመገመበት ወቅት እንደተመላከተው፣ መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ በመጀመራቸው ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው የደመወዝ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ተደርጓል።

ሆኖም ሠራተኞች የሥራ ሰዓትን አክብሮ በመግባት ረገድ ውስን ክፍተቶች መኖራቸው በግምገማው ተነስቷል።

በንግዱ ዘርፍም በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንቅስቃሴዎች ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለሳቸው፣ እንዲሁም መሠረታዊ ሸቀጦች እና ነዳጅ ወደ ከተማዋ መግባት መጀመራቸው የተሻለ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አድርጓል።

ከዚህ ባለፈ የመንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ የከተማዋን አውቶቡስ ተርሚናል በመክፈት፣ ወደ መቐለ የሚገቡ እና የሚወጡ ጉዞዎች ሰላማዊ እና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ከፍተኛ ሥራ ማከናወኑ ተገልጿል።

በጸጥታው ዘርፍ ከባድ ወንጀሎችን በመከላከል የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ፣ ወጣቶችን በማደራጀት እና ሕዝቡን በማሳተፍ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት አካባቢን የመጠበቅ ሥራዎች መከናወናቸው ተጠቅሷል።

ሁሉም ቢሮዎች የተቀናጀ አሠራርን በመከተል ሕዝቡን በተሻለ ብቃትና ትጋት እንዲያገለግሉ ከንቲባው አሳስበዋል።

በአስማረ ብርሃኑ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: