በትግራይ ክልል አሁን ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ ለሥልጣን ሳይሆን፣ ክልሉን በቀጣዮቹ አምስት ወራት ለምርጫ ለማዘጋጀት መሆኑን በክልሉ ባለአደራ አስተዳደር የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሺሻይ አማረ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ከንቲባው ባለፉት 30 ቀናት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በትግራይ ሰላም ኃይል እና በሕዝቡ ትብብር በከተማዋ የወንጀል ድርጊቶች እየቀነሱ መምጣታቸውን አስታውቀዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመቀናጀት 80 በመቶ የሚሆኑ ችግሮችን በእርቀ ሰላም ለመፍታት፣ ከባድ ወንጀል የፈጸሙትን ደግሞ በህግ እንዲጠየቁ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ መደበኛ እንቅስቃሴን ለመመለስ የትራንስፖርት፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባታቸውን የጠቆሙት ከንቲባው፣ ለጸረ ሰላም ኃይሉ ተከማችቶ የነበረ ፍጆታ እቃዎችን ለሕዝብ መከፋፈል መጀመሩንና አገልግሎቶች ሰጭ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
እየተደረጉ ያሉ የሕዝብ ውይይቶች ሕዝቡ እንዲገናኝ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
አሁን እየተሠራ ያለው ሥራ ለሥልጣን ሳይሆን፣ ክልሉን በቀጣዮቹ አምስት ወራት ለምርጫ ለማዘጋጀት መሆኑን በማስገንዘብ፣ ሕዝቡ ከተሳሳተ መረጃ ራሱን እንዲጠብቅና ዓለም አቀፍ ለጋሾችም ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በአስማረ ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: