Search

የአፍሪካን የቴክኖሎጂ መሪነት ለመጨበጥ የሚደረግ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ጉዞ

ማክሰኞ ኅዳር 08, 2019 132

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለቤት የሆነችው እና አብዛኛው ቁጥር ወጣት የሆነባት ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገቷን በቴክኖሎጂ እና በዲጂታል ሽግግር ለማዘመን መሠረታዊ ለውጦችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በመላው አህጉሪቱ የቴክኖሎጂ እና የኢኖቬሽን ማዕከል የመሆን ራዕይ ሰንቃ እየተንቀሳቀሰች ያለችው ኢትዮጵያ፣ ዲጂታል ሽግግርን የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የሕልውና፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የዘላቂ ልማት ቁልፍ መሣሪያ አድርጋ ወስዳዋለች።

የአፍሪካ የቴክኖሎጂ መሪነት በአንድ ዘርፍ ብቻ በሚመዘን ስኬት የሚገኝ ሳይሆን፣ በፈጠራ አቅም፣ በሰው ኃይል ክህሎት፣ በጠንካራ መሠረተ ልማት እና በዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚለካ ነው። ኢትዮጵያ ይህንን ሚዛን ለመጠበቅ የጀመረችው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ዛሬ ላይ ተጨባጭ ፍሬዎችን ማፍራት ጀምሯል።

ለቴክኖሎጂ ጉዟችን መሠረት የጣለው "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" እና ወደ ሥራ የገባው "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂዎች የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የጀርባ አጥንት ናቸው። እነዚህ ፖሊሲዎች ግብርናውን፣ ማኑፋክቸሪንግን፣ ቱሪዝምን እና የአገልግሎት ዘርፉን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀረጹ ናቸው።

ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ የቴሌኮም ዘርፉን ለውድድር ክፍት የማድረግ ትልቅ ስትራቴጂያዊ እርምጃ ተወስዷል። አንጋፋው ኢትዮ ቴሌኮም የ5ጂ (5G) ኔትወርክን በአዲስ አበባ እና በዋና ዋና የክልል ከተሞች በማስፋፋት የቴክኖሎጂ አድማሱን ሲያሰፋ፣ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ ገበያ መግባቱ ጤናማ ውድድርን ፈጥሯል። በዚህም የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት አድጓል።

ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገው "ፋይዳ" ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የዲጂታል ዘርፉን መሠረት ለማጽናት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ፋይዳ የፋይናንስ አካታችነትን ከማሳደግ ባለፈ፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል (እንደ "መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባሉ አሠራሮች) ቀልጣፋ እና ከሙስና የጸዳ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ራሱን የቻለ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ተቋም በማቋቋም ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች። ተቋሙ በጤናው ዘርፍ በሽታዎችን አስቀድሞ በመመርመር፣ በግብርና የሰብል በሽታዎችን በመለየት እና የአፈር ለምነትን በመተንተን እንዲሁም በሀገር በቀል ቋንቋዎች (በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ እና በሌሎችም) የሚሠሩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ላይ ይገኛል። ይህም የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ አንጻር ትልቅ ትርጉም አለው።

ያለ በቂ የሰው ኃይል ክህሎት የመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻውን የቴክኖሎጂ መሪነትን ሊያረጋግጥ አይችልም። ይህንን የተረዳው መንግሥት ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጋር በመተባበር ይፋ ያደረገው የ"አምስት ሚሊዮን ኮደርስ" ኢኒሼቲቭ የትውልድ ግንባታ ታሪካዊ እርምጃ ነው።

ይህ መርሐ ግብር በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በአንድሮይድ መተግበሪያ ግንባታ ዙሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና በነፃ በመስጠት ላይ ይገኛል።

ዋና ዓላማውም የኢትዮጵያ ወጣቶች በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የዲጂታል የሥራ ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ እና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን እንዲመሠርቱ ማስቻል ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬ የምትዘራው የዲጂታል ዘር ነገ ለቀጣዩ ትውልድ የብልጽግና መሠረት ነው። በርካታ ወጣት የሰው ኃይል፣ እያደገ የመጣ የቴሌኮም መሠረተ ልማት እና ቁርጠኛ የፖሊሲ አቅጣጫ ተደምረው ኢትዮጵያን በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ካርታ ላይ ጎልታ እንድትወጣ እያደረጓት ነው።

የቴክኖሎጂ መሪነት የሚለካው የአርሶ አደሩን ምርት ሲያሳድግ፣ የተማሪውን ዕውቀት ሲያሰፋ፣ የታካሚውን ሕይወት ሲታደግ እና የዜጎችን ክብርና ሉዓላዊነት ሲያስጠብቅ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ጎዳና ላይ ጉዞዋን ጀምራለች፤ መዳረሻዋም በፈጠራ የበለጸገች፣ ለዜጎቿ የምትመች እና ለአፍሪካ ምሳሌ የምትሆን ዲጂታል ሀገር መገንባት ነው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: