ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ7ኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በኢንዱስትሪ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በኢነርጂ እና በቱሪዝም ዘርፎች ተጨባጭ እመርታ መመዝገቡን አስታውቀዋል።
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዕድገት ማሳየት መጀመሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን ዕድገት በበቂ ደረጃ የሚለካ ሥርዓት እንዳልነበረ አመልክተዋል።
አረንጓዴ ዐሻራን በተመለከተ በሰጡት ገለጻ፣ በበርካታ ፍራፍሬዎች እና በቡና ምርት የመጣውን እመርታ አንስተዋል።
ቀደም ሲል ኢኮኖሚው ይህንን እድገት በበቂ ደረጃ ከልሶ ያቀፈ እንዳልነበረ እና አሁን ላይ በአዲሱ የ'ጂዲፒ' ስሌት መካተቱን ጠቅሰዋል።
ከኢነርጂ አንጻር ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአሰላ እና የአይሻ የንፋስ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም የገናሌ ዳዋ እና የሕዳሴ ግድቦች መመረቃቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከፀሐይ ኃይል አንጻር በርከት ባሉ የገጠር ኮሪደር ልማቶች 'ኦፍ-ግሪድ የሶላር ሲስተም' እየተገነባ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብዙ መሠረተ ልማቶች በመገንባት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።
ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ሲካሄድ ሌላ ጉባኤ በተጓዳኝ መካሄዱን አስታውሰዋል።
ይህም በአንድ ቀን ሁለት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለማካሄድ የሚያስችል ብቃት መገንባቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: