Search

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የአዲስ አበባን የስፖርት ቱሪዝም እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃበት ታላቅ መድረክ

ዓርብ ኅዳር 11, 2019 99

በየዓመቱ የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት የሚያደምቀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ ዘንድሮም 60 ሺህ ተሳታፊዎችን በማሰባሰብ የጎዳና ላይ ትዕይንቱን ዳግም ለማድመቅ ዝግጅቱን አጠናቅቋል።

ይህ ግዙፍ ሁነት የኢትዮጵያን የስፖርት ቱሪዝም አቅም ለዓለም የሚያስተዋውቅ እና የመዲናዋን ኢኮኖሚ የሚያነቃቃ ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ ቀጥሏል።

ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውና የአፍሪካ ትልቁ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የሆነው ታላቁ ሩጫ፣ ዓለም አቀፍ ሯጮችን፣ የስፖርት አፍቃሪያንን፣ ዲፕሎማቶችን እና ቱሪስቶችን ወደ አዲስ አበባ የሚስብ ታላቅ መድረክ ነው። 

በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ ጊዜ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ሲተምሙ የሚፈጠረው ደማቅ የፌስቲቫል ድባብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ስሜት ይፈጥራል።

ለውጭ ጎብኚዎችም ከኢትዮጵያውያን የረጅም ርቀት ጀግኖች ጋር ትከሻ ለትከሻ ተገፋፍቶ የመሮጥ ብርቅዬ አጋጣሚን ይሰጣል።

ይህም ኢትዮጵያ "የሯጮች ምድር" በሚል የገነባችውን በጎ ገጽታ በተግባር የሚያረጋግጥ እና የስፖርት ቱሪዝም ዘርፉን በቀጥታ የሚያሳድግ ነው።

የ60 ሺህ ተሳታፊዎች መሰባሰብ ለአዲስ አበባ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ይዞ ይመጣል።

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች እና ከመላው ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶች መበራከት ለከተማዋ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች እና የባህል ምሽት ቤቶች ሰፊ የገበያ ዕድል ይፈጥራል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ የስፖርት ትጥቅ አቅራቢዎች፣ የቅርጻ ቅርጽ እና የባህል አልባሳት ሻጮች እንዲሁም አስጎብኚ ድርጅቶች ከፍተኛ የደንበኞች ፍሰት ያስተናግዳሉ።

ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር፣ ውድድሩ በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የሚኖረው ሰፊ ሽፋን አዲስ አበባ ለዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች እና ለቱሪዝም ምቹ የሆነች ሰላማዊ መዲና መሆኗን ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ይህንን ያህል ሕዝብ በአንድ መድረክ በሰላም ማስተናገድ የኢትዮጵያን የኹነት አዘገጃጀት ብቃት እና እንግዳ ተቀባይነት የሚያሳይ ተጨባጭ ማሳያ ነው።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝምን ከማሳደግ እና በጎ አድራጎትን ከመደገፍ ባለፈ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ የጤና እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባህል እንዲዳብር የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በዚህ ታሪካዊ ቀን ሲደምቁ፣ ኢትዮጵያ በስፖርቱ ዓለም ያላትን የበላይነት ብቻ ሳይሆን በቱሪዝም እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም ዳግም ታሳያለች።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: