ወጣት እሸቱ ሶራቶ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ ሲሆን፤ ከ7 ዓመታት አስቸጋሪ የስደት ኑሮ በኋላ በሀገሩ የተረጋጋና አስደሳች ሕይወት እየመራ መሆኑን ይናገራል።
ከዓመታት በፊት በአቻ ግፊት የተሻለ ሕይወት ፍለጋ መዳረሻውን አውስትራሊያ አድርጎ ከእናት ሀገሩ በኬኒያ በኩል መሰደዱን ያስታውሳል።
ሆኖም ጉዞው እንዳሰበው አልሆነም፤ ከዚህም የተነሳ ለ7 ድፍን ዓመታት ካሰበበት ሳይደርስ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሲንከራተት ቆይቷል።
ረሀብ፣ ጥም፣ በጀልባ ላይ ለበርካታ ቀናት መቆየት እና በሕገ-ወጥ ደላላዎች የሚፈፀሙ ክህደቶች የስደት ሕይወቱን አስቸጋሪ እንዳደረጉበት ይገልፃል።
ወጣት እሸቱ ስደት በቃኝ ብሎ ከዛንዚባር ወደ ሀገሩ ከተመለሰበት ጊዜ አንስቶ ለወጣቶች የስደትን አስከፊ ገፅታ ከተሞክሮው እያጋራ ይገኛል።
ከዚህ ባሻገር ከስደት መልስ በሀገሩ በመሥራት በሕይወቱ ላይ ያመጣው ለውጥም በሀገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ሆኗል።
በ2010 ዓ.ም ከጓደኞቹ ጋር በማህበር ተደራጅተው የከፈቱት የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል 5 ቋሚ እና 7 ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ከዚህ ጎን ለጎን የከብት እርባታ በመጀመር የ14 የወተት ላሞች ባለቤት መሆን የቻሉት ወጣቶቹ፤ ከላሞቹ የሚገኘውን ወተት ለደንበኞቻቸው ጭምር በማከፋፈል ላይ ይገኛሉ።
ወጣት እሸቱ በግሉም መሀል ሶዶ ከተማ ላይ የጀበና ቡና መሸጫ የከፈተ ሲሆን፤ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማውጣት በ8 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የከብት እርባታ ሥራ ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቅቋል። በዚህም ለ100 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዷል።
ወጣቶች በርትተው ከሰሩ ኢትዮጵያ ለብዙዎች የሚተርፍ ሀብት አላት ሲል ወጣት እሸቱ ምክሩን ለግሷል።
በተመስገን ተስፋዬ
#EBCdotstream #Youths #Entrepreneurship #Migration