ከነሐሴ 24 እስከ ነሐሴ 29 የኢትዮጵያን ይግዙ በሚል 168 የንግድ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽን እና ባዛር በጥራት መንደር እንደሚካሄደ ተገለፀ። የኢትዮጵያ ልዩ የንግድ ሳምንቱ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከናወን ነው።
መግለጫውን የሰጡት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሐኪም ሙሉ (ዶ/ር)፥ የንግድ ሳምንቱ ዋነኛ ዓላማ የኢትዮጵያን ምርቶች ማስተዋወቅ እንዲሁም የምርቶቹን ጥራት እና ተወዳዳሪነት ማሳየት ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ኤግዚቢሽኑ በሀገር ምርት የመጠቀም ባህልን ለማዳበር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል።
የሀገር ምርትን መግዛት እና መጠቀም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉትም አብራርተው፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ፣ የንግድ ሚዛን ክፍተትን ለማጥበብ፣ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር እና ገቢን የመሰብሰብ አቅምን ለማጎልበት አይተኬ ሚና አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ምርት እና አገልግሎት መግዛት ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሚናው የላቀ በመሆኑ የንግድ ሳምንቱን ማካሄድ አስፈልጓል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ህብረተሰቡም የሀገሩን ምርት በመግዛት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የንግድ ሳምንቱ ትላልቅ ሁነቶች የሚከናወኑበት ሲሆን፤ ሸማቾች የግብርና እና ሌሎች ምርቶችን ከነፃ ገበያው ባነሰ ዋጋ መገብየት የሚችሉበት እንዲሁም የፓናል ውይይት መድረኮች የሚካሄዱበት መሆኑ ተገልጿል።
የንግዱ ማህበረሰብ በዚህ ታላቅ የንግድ ሳምንት ላይ ምርቶቻቸውን ይዘው እንዲቀርቡ፤ እንዲሁም ህብረተሰቡም ከዚህ ኤግዚቢሽን እና ባዛር ምርቶችን እንዲገዛ ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል።
በኤዶም አማረ
#ኢቢሲዶትስትሪም #የንግድሳምንት #የጥራትመንደር #የኢትዮጵያንይግዙ